ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ አካሄደ፡፡

ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ በሚሊኒየም ፓርክ ከተቋሙና ከአካባቢው ማህበረሰብ ተወካዮች ጋር በ03/12/13 ዓ.ም አካሄደ፡፡
የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ብርሃነመስቀል ጠና፤ የዚህን ዓመት ኢትዮጵያን እናልብስ አሻራችንንም እናስቀምጥ በሚል መርህ የዚህን ዓመት የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ተቋማችን በተለያዩ ሁለት ፕሮግራሞች ሲያከናውን መቆየቱንና አሁንም ከሴኔት አባላት፣ ከመምህራንና አስተዳደር ሠራተኞች፣ እንዲሁም ከመጀመሪያ ዓመት መደበኛ ተማሪዎችና ከአካባቢው የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር በመቀናጀት የተደረገ በመሆኑ ደስታ ይሰማኛል በማለት ንግግራቸውን ጀምረዋል፡፡ በመቀጠልም ዛሬ የምንተክለው ችግኝ ለነገ በእያንዳንዳችን ሕይወት ላይ ትልቅ ለውጥ የሚያስከትል በመሆኑ መፅደቁን በዚያው ልክ እየተከታተልን የሃገራችንን ልምላሜ ማረጋገጥ ይገባናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
እንደ ዶ/ር ብርሃነመስቀል ገለፃ፤ የሃገራችንን ሥነ ምህዳሯንና ዙሪያዋን በጋራ ለመጠበቅ ሲባል በኃላፊነት እንደተከልነው ሁሉ በኃላፊነት መንከባከቡንም እንዲሁ ማድረግ ይገባናል ሲሉ አሳስበዋል፡፡ ተተኪ ትውልድ የሆናችሁ የመደበኛው የመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎች ከአካባቢው የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር አደራ ለመቀበልና የኔ የምትሉትን አሻራም ለማስቀመጥ እዚህ በመገኘታችሁ ኩራት ሊሰማችሁ ይገባል ብለዋል፡፡
የኮተቤና አካባቢው የማኅበረሰብ ክፍሎች ተወካይ አቶ ወንድሙ ግዛው መርሃ ግብሩን በማስመልከት ባስተላለፉት መልዕክት እንዳሉት፤ የኮተቤና አካባቢው ማኅበረሰብ ዋነኛ የጋራ ሃብታችን የሆነው ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ብቻ ነው ብለዋል፡፡ አያይዘውም ሲገልፁ፤ ዛሬ ላይ ሁላችንም አንድ ችግኝ ስንተክል ጥላቻን፣ ዘረኝነትን፣ ምቀኝነትና ተንኮለኝነትን ከውስጣችን ነቅለን መጣል አለብን ሲሉ ተናግረዋል፡፡
መርሃ ግብሩ የቅድመ ምረቃ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በሆኑት በዶ/ር መስፍን አበበ ቢሮ መሪነት መከናወኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡
የኮርፖሬት ኮሚኒኬሽን ዳይሬክቶሬት
Posted in Office of the Communication Affairs.

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *