የኮሜዩ-ዳግማዊ ምኒልክ ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የካንሰር የጨረር ህክምና ትምህርት ከባለድርሻው አካላት ጋር በመተባበር በሀገራችን ለመጀመርያ ጊዜ የሚሰጥ መሆኑ ተገለጸ፡፡

የኤፌድሪ ጤና ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ሊያ ታደሰ፣ የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ዳግማዊ ምኒልክ ጤና ሳይንስ ኮሌጅና አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፣ ከጤና ሚንስቴር እና ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚንስቴር ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የሬዲዮቴራፒ ሕክምና ቴክኒሻኖች (RTT) የሥልጠና መርሃ ግብር መጀመራቸው ለመላው ሀገራችን በማህበራዊ ሚዲያ እጅግ እንዳስደሰታቸው  ገልጸው፣ ሥርዓተ-ትምህርቱ፣ በተለያዩ አካላት አጋርነት የተዘጋጀ፣ አሁን በስራ ላይ ያሉ ዲፕሎማ ራዲዮግራፈሮችን በመጀመሪያ ዲግሪ (RTT) ለመመረቅ የሚያስችል የ2 ዓመት ፕሮግራም መሆኑን ገልጸዋል። ለዚህም መርኃ-ግብሩን ከግብ ላደረሱ አካላትን ሁሉ አመስግነዋል፡፡

ዶ/ር ብርሃነመስቀል ጠና በበኩላቸው ተቋሙ ቀደም ብሎ በሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ደረጃ ሲዋቀር፣ በአዲስ አስተሳሰብና ቴክኖሎጂ የተሻለ አቅምን በመፍጠር ለከተማችን ማህበረሰብ ብቁ አገልግሎትን መስጠት መሆኑን አውስተው፣ በሽታው በህዝባችን ላይ የፈጠረው ጉዳት በቁጭት እንድናስብ አድርጎናል፤ ለዚህም ዩኒቨርሲቲያችን ለመፍትሄው በትምህርት፣ ጥናትና ምርምር ለማምጣት ይህ የሬዲዮቴራፒ ሕክምና ትምህርት አይነተኛ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የዳግማዊ ምኒሊክ ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን አቶ ኩማ ጌታሁን ይህ የትምህርት ዘርፍ በሃገር አቀፍም ሆነ በተቋማችን ደረጃ እየተሰጠ ያለው ለመጀመሪያ ጊዜ በመሆኑና ከሁሉም ቀዳሚ በመሆናችን ሊያስመሰግነን እንደሚገባም ገልጸው፣ በጥናትና ምርምር በማስደገፍ፣ በሃገር አቀፍ ደረጃ እየጨመረ  ያለውን የካንሰር በሽታ በከፍተኛ ደረጃ በመቆጣጠር ለመፍትሄውም ሁሉም ባለድርሻ አካላት መተባበር እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡                          

በክሊንተን አክሰስ ኢንሼቲቭ የካንሰር ፕሮግራም ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር ያሬድ ጥላሁን መርሃ ግብሩን በማስመልከት እንዳሉት፤ ድርጅታቸው የጨረር ህክምና ላይ ከፍተኛ ልምድ ስላለውና ራሳቸውም በሥራው ላይ በመሆናቸው ሥርዓተ ትምህሩቱ በምን መልኩ ቢሻሻል የበለጠ ውጤት እንደሚያስገኝ ከልምዳቸው አንፃር አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

የ Radiotherapy Technology ትምህርት ክፍል ኃላፊ ወ/ሮ መታደል ኃይሉ እንዳሉት፤ ይህ ትምህርት በሃገራችን አዲስ እንደመሆኑ መጠን በ2013 ዓ.ም አዲስ ተማሪዎችን ተቀብለን ማስተማር ስንጀምር በይዘቶቹ ላይ የተወሰኑ ክፍተቶች ስለተመለከትንና የምናስተምራቸውም ተማሪዎች ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ ሲባል ሥርዓተ ትምህርቱን ለመከለስ ተገደናል ብለዋል፡፡

በማጠቃለያም፣ ክብርት ወ/ሮ ሰሐረላ አብቡላሂ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ፣ በቀጣይነትም በዘርፉ አግባብነት ያላቸው የሙያው ባለቤቶች በሃገር አቀፍ ደረጃ በቂ ዝግጅት በማድረግ የሙያ ዘርፉ በሚፈልገውን ባለሙያዎች በማፍራት ችግሩን መቅረፍ እንደሚቻል ይታመናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የኮርፖሬት ኮሚኒኬሽን ዳይሬክቶሬት

   

Posted in Office of the Communication Affairs.

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *