ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ በቦረና በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ አደረገ።

ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ በኦሮሚያ ክልል በቦረና ዞን የዝናብ ዕጥረት ባስከተለው ድርቅ ከፍተኛ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ምግብ ነክና የውሃ መያዣ ቁሳቁሶች እንዲሁም ለቤት እንስሳቱ መኖ በድምሩ ወደ አንድ ሚሊዮን ብር የሚጠጋ የዓይነት ድጋፍ አድርጓል፡፡
የዩኒቨርሲቲውን ማህበረሰብ በመወከል ለቦረና ዞን አስተዳደር ድጋፉን ያስረከቡት አቶ አባይ በላይሁን በርክክቡ ወቅት ባደረጉት ንግግር፣ ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ይህንን ድጋፍ በድርቁ ለተጎዱ ወገኖች ሲያደርግ አጋርነቱን ለማሳየት እንደሆነ ገልፀው ዩኒቨርሲቲው በቀጣይም ችግሩን በዘለቄታዊነት ለመፍታት ከአካባቢው ማህበረሰብና ከሌሎች ተቋማት ጋር በመተባበር እንደሚሰራ አስገንዝበዋል፡፡
እርዳታውን የተረከቡት የቦረና ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አብዱሰላም ዋሪዮ በበኩላቸው በድርቁ ለተጎዱ ወገኖች የተደረገውን ድጋፍ በማድነቅ ለኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ማኔጅመንት እና ለመላው የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ በመቀጠልም ድጋፉ በአሁኑ ሰዓት የአርብቶ አደሩን እና የእንስሳቱን ህይወት ለመታደግ እያደረግን ለምንገኘው ርብርብ ትልቅ እገዛ እንደሚያደርግ ገልጸው፣ የዝናቡ ዑደት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ በመምጣቱና በአካባቢው ላይም አስከፊ ጉዳት እያደረሰ በመሆኑ፣ ችግሩን በዘቄታዊነት ለመፍታት በቴክኖሎጂ መታገዘ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ባለፉት ሁለት ዓመታት በሃገሪቱ በተፈጠሩ ሰው ሰራሽና ተፈጥሮአዊ ችግሮች ምክንያት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳቶች ለደረሰባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች አጠቃላይ የ24 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ያደረገ ሲሆን፣ በቅርቡም በደብረብርሃን ከተማ ተጠልለው ለሚገኙ ተፈናቃዮች የ1.2 ሚሊዮን ብር ዕርዳታ ማድረጉ ይታወሳል።

                                           የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት

 

Posted in Office of the Communication Affairs.

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *