ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ለኮተቤ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የማስተማሪያ ቁስ ድጋፍ አደረገ

ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የመማር ማስተማር ሂደትን የሚያግዙ ቀለማቸው ነጭ እና አረንጓዴ የሆኑ ሃያ የማስተማሪያ ቦርዶችን ለኮተቤ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ሚያዝያ 1 ቀን 2014 ዓ.ም በትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ በመገኘት  አበርክቷል፡፡

ድጋፉን በቦታው በመገኘት ለትምህርት ቤቱ አስተዳደር ያስረከቡት የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሽመልስ ዘውዴ፤ ተቋማችን አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ በተማሪዎች ቁጥር መጨመርና በሌሎች ምክንያቶች የመማሪያ ክፍል ጥበት ሲገጥመው ወደ ኮተቤ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት በመሄድ የመማር ማስተማሩን ተግባር እንደሚከውን ገልፀው፤ ዛሬ የተሰጠው ድጋፍም በትምህርት ቤቱ አመራርና በእኛ መምህራን በኩል የማስተማሪያ ቦርድ ችግር መኖሩ በተጠቆመው መሠረት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ከትምህርት ቤቱ ጋር ባለው መልካም ግንኙነት እና ከቅርበቱም የተነሳ እስካሁን ድረስ በጋራ የተለያዩ ሥራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ የገለጹ ሲሆን፤ በቀጣይም ትምህርት ቤቱን እንደሞዴል በመውሰድ የተለያዩ የማኅበረሰብ አገልግሎት ስራዎችን እንደሚያከናውን ተናግረዋል፡፡

የኮተቤ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህርት የሆኑት ወ/ሮ ዓለም አበበ ድጋፉን በተረከቡበት ወቅት እንዳሉት፤ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ጥቁር ሰሌዳዎቻችን እጅግ በመበላሸታቸው ምክንያት የመማር ማስተማሩን ተግባር ለመከወን ችግር እንደነበረባቸው አውስተው፤ አሁን ግን በቅርበት የሚገኘው ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የተለዩና አዳዲስ የማስተማሪያ ሰሌዳዎችን በስጦታ ስላበረከተልን የገጠመን የጥቁር ሰሌዳ ችግር ሙሉ ለሙሉ ተወግዶልናል ብለዋል። በመቀጠልም  ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የተለያዩ የምርምርና የማማከር ሥራዎችን በትምህርት ቤቱ እያከናወነ እንደሆነ የገለጹት ርዕሰ መምህርቷ፤ በቀጣይም በተቋማችን ውስጥ የሚስተዋሉ ለተማሪዎች መመገቢያ የሚሆኑ ወንበሮች፣ ያገለገሉ ኮምፒውተሮችና የሌሎችም ቁሳቁሶች ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ቃል እንደተገባላቸው ተናግረዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት

Posted in Office of the Communication Affairs.

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *