የፀረ-ሙስና ዳይሬክቶሬት የሥራ ስነ-ምግባርና ተቋማዊ ባህል ግንባታ ላይ ያተኮረ ስልጠና አካሄደ፡፡

የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ የፀረ-ሙስና ዳይሬክቶሬት “በትምህርት ተቋማት የሥራ ስነ-ምግባርና ተቋማዊ ባህል ግንባታ” በሚል ርዕስ ለአስተዳደር ሠራተኞችና ለአመራሮች ከስነ-ምግባርና ስነ-ዜጋ ትምህርት ክፍል በተጋበዙ መምህራን መጋቢት 28 እና 29/2014 ዓ.ም ስልጠና ሰጥቷል።
በስልጠናው የመክፈቻ ንግግር ያሰሙት የአስተዳደርና ተማሪዎች አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ተስፋዬ ነጋሽ፣ በስነ-ምግባርና በተቋማዊ ባህል ግንባታ ላይ ያተኮረው ስልጠና ሠራተኞችም ሆኑ ፈፃሚ አካላት ህግና ደንብን ተከትለው ለህዝብና ለሀገር ጥቅም መስራት የሚገባቸውን ስራዎች በአግባቡ ለመስራት የሚያስችላቸውን ግንዛቤ ያስጨብጣቸዋል ብለዋል፡፡ ስልጠናው በሠራተኛውም ሆነ በዩኒቨርሲቲው አመራሮች ዘንድ የስነ-ምግባርና የተቋማዊ ባህል ግንባታ ግንዛቤ ከማስጨበጡም በተጨማሪ፣ ሥራን በጥራትና በፍጥነት በመስራት ረገድ ከአስተሳሰብ ጀምሮ ተቋማዊ ለውጥ እስከማምጣት የሚደርስ ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ይታመናል ሲሉ ገልፀዋል፡፡
ስልጠናውን የሰጡት የስነ-ምግባርና ስነ-ዜጋ ትምህርት ክፍል መምህርት የሆኑት ወ/ሮ ገነት አበበ በዚሁ ጊዜ ባቀረቡት የውይይት መነሻ ጽሑፍ የስልጠናው ዋና ዓላማ የሥራ ሥነ-ምግባር፣ የመልካም አስተዳደር፣ የተቋማዊ ባህል እና ሞራላዊ ምክንያታዊነት እንዲሁም የሥራ ውጤታማነት በትምህርት ተቋማት ውስጥ ማስገንዘብ መሆኑን ጠቁመው፣ ከስልጠናው በኋላም ሃላፊነትን የማወቅና በአግባቡ የመወጣት፣ የሥራ ተነሳሽነትና የዩኒቨርሲቲውን የሥራ ባህል እንደገና በመቃኘት ሰልጣኞች ጥሩ የሥራ ባህል እንዲያዳብሩ የሚያስችል መሆኑን ገልፀዋል። የሥራ ላይ ስነ-ምግባር መርሆዎች ቅንነት፣ ታማኝነት፣ ግልፅነት፣ ተጠያቂነት፣ ሀቀኝነት፣ ምስጢር መጠበቅ፣ አለማዳላት እና ህግን ማክበር መሆናቸውን የዘረዘሩት መምህርቷ፣ የተቋሙ ድክመትም ሆነ ጥንካሬ የጋራ በመሆኑ፣ ተቋማዊ ባህል ለመገንባት ሁለገብ ተሳትፎ ያስፈልጋል ብለዋል።
ስልጠናው በሁለት ምድብ የተከፈለ ሲሆን፣ በሁለተኛው ዙርም የስነ-ምግባርና ስነ-ዜጋ ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት አቶ እያሱ በሬንቶ የትምህርታዊ ውይይት መነሻ ሃሳብ አቅርበው በሰራተኞቹና በአመራሮቹ ተመሳሳይ ውይይት ተካሂዷል።
                                                               የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት
Posted in Office of the Communication Affairs.

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *