ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ፋካልቲ የሚያዘጋጀው የእውቀት ማጋራት መርሐ ግብር መጠናከርና በሌሎች መለመድ እንዳለበት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ገለፁ።

የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ፋካልቲ ሦስተኛውን የእውቀት ማጋራት መርሐ-ግብር በ11/08/2014ዓ.ም ባካሄደበት ወቅት የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ብርሃነመስቀል ጠና፣ ፋካልቲው የሚያዘጋጀው ወርሃዊ የእውቀት ማጋራት መርሐ-ግብር እንደጥሩ ልምድ ተወስዶ ከዚህ የበለጠ በሀገር ዓቀፍ ደረጃ ማደግ እና መስፋት እንዳለበት ገልፀዋል። ተማሪዎችም እውቀት የሚቀስሙበት በመሆኑ ልምዱ በሁሉም ፋካልቲዎች መለመድ አለበት ብለዋል።
የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ሽመልሽ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር፣ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ፋካልቲ ፈር ቀዳጅ ሆኖ ብዙ ጥናታዊ ጽሑፎችን እና መድረኮችን በተከታታይ በማዘጋጀት በግንባር ቀደምትነት የሚተጋ ፋካልቲ በመሆኑ ለማመስገን እወዳለሁ ካሉ በኋላ፣ የዛሬው ውይይት ዓለም ዓቀፋዊ እና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የተዘጋጀ እንደመሆኑ መጠን ውይይቱን አስፈላጊና የተለየ እውቀት የሚገኝበት ነው ሲሉ ተናግረዋል። ይህ ዓይነቱን እውቀት የማጋራት መድረክ የተወሰኑት ፋካልቲዎች የጀመሩ ቢሆንም የተቀሩት ፋካልቲዎች ከዚህ አይነቱ መድረክ ተምረው ብዙ መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
የቢ.ኢ.ፋ ዲን የሆኑት ዶ/ር ኃይለሚካኤል ሙሌ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ባሰሙበት ወቅት፣ በፋካልቲያችን ደረጃ አቅደን ከምንሰራቸው ሥራዎች ውስጥ አንዱ ይህ የእውቀት ማጋራት ሲሆን፣ በቀጣይ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎትን የተመለከቱ ሁለት መድረኮች በተከታታይ እንደሚቀርቡና የኒውስሌተር ዝግጅትም እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል። ከዚህም በተጨማሪ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ጉዳይ በአብዛኛው የጋራ ጉዳይ በመሆኑ፣ ሰፋ ባለ መድረክ የሚያወያዩ ሀገራዊ እና ዓለምዓቀፋዊ አጀንዳዎችን በመቅረፅ እንደሚቀርቡ አሳውቀዋል።
በመርሐ-ግብሩ ላይ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ እንዲሁም የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት በዓለም ኢኮኖሚ ላይ ያስከተሉትን ተፅዕኖ እና ተያያዥ ጉዳዮችን የተመለከቱ ሁለት የውይይት መነሻ ጽሑፎች የፋካልቲው መምህራን በሆኑት በአቶ ዮናስ አብርሃ እና በአቶ አብደላ ቆሳ ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
                                                           የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት
Posted in Office of the Communication Affairs.

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *