ኮትዩ ለአብርኆት ቤተ መጻሕፍት መጽሐፍትን በስጦታ አበረከተ።

ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለተቋቋመው ለአብርኆት ቤተ መጻሕፍት፣ መጽሐፍትን እንዲያሰባስብ ኃላፊነት በተሰጠው በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በኩል ግንቦት 2 ቀን 2014 ዓ.ም ከጉድለቱ ሦስት መቶ ሃምሳ አምስት መጻሕፍትን በስጦታ አበርክቷል።
የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ብርሃነመስቀል ጠና ስጦታውን በማስመልከት እንደተናገሩት፣ ተቋማችን ከሁሉም የትምህርት ዓይነቶች የተውጣጡ በግምት ዋጋቸው ሰባት መቶ ሰባ ሺህ ብር የሚሆን ሦስት መቶ ሃምሳ አምስት መጻሕፍትን ለአብርኆት ቤተ መጻሕፍት በስጦታ ማበርከቱን ገልጸው፣ መጽሐፍት በትውልድ ቅብብሎሽ ለዘመናት ስለሚቆዩ ስጦታው ለትውልድ የተበረከተ እንደሆነ አድርጎ መውሰድ ይቻላል ብለዋል። ፕሬዚዳንቱ አያይዘውም አንባቢ ትውልድ ለመገንባት በሀገር ደረጃ በቂ ቤተ መጻሕፍት ሊኖሩ እንደሚገባ የገለጹ ሲሆን የተሠጡት መጽሐፍት ከአንደኛው ቤተመጽሐፍታችን ወደሁለተኛው ቤተመጽሐፍት እንደተሠጡ የሚቆጠር ነው ብለዋል። አያይዘው እንደገለፁት የሕዝባችንን አብሮነት እውን ለማድረግም የተማረ ትውልድ የመገንባትን አስፈላጊነት እንዲሁም ሃሳብን በጉልበት ከመሞገት ይልቅ በንባብ በታገዘ ዕውቀት መሞገት፣ ከስሜታዊነት ይልቅ የሰከነ ሕይወት ለመኖር እንደሚያስችል አብራርተዋል። የአብርኆት ቤተ መጻሕፍት እንደ ስሙ ሁሉ ትልቅ ሆኖ በሀገር አቀፍ ደረጃ እንዲታወቅ ሁላችንም የድርሻችንን መወጣት እንደሚገባንና ለኅብረተሰባችንም እንዲህ ዓይነት ቤተ መጻሕፍቶችን በብዛት መገንባት እንደሚገባን ፕሬዝዳንቱ አሳስበዋል።
የዩኒቨርሲቲው የቤተ መጻሕፍትና አካዳሚክ ዶክመንቴሽን ዳይሬክተር አቶ ገብረመስቀል ግርማ የመጻሕፍት ስጦታውን በማስመልከት እንዳሉት፣ አብርኆት ቤተ መጻሕፍት ሁሉንም የማኅበረሰብ ክፍል ለማገልገል ተብሎ የተቋቋመ በመሆኑ የተቋማችን የቤተ መጻሕፍት ተጠቃሚዎች በስፋት የሚገለገሉባቸውን መጻሕፍት ለዚህ የሕዝብ ቤተ መጻሕፍት አካፍለናል ብለዋል። የተደረገው ስጦታም በሀገራዊ ጉዳይ ላይ ካለን ላይ የማካፈል እና በጋራ የመቆምን አስፈላጊነት ያሳየ ከመሆኑም ባሻገር፣ የማኅበረሰቡን የአስተሳሰብ ደረጃ በመገንባት በኩል ሰፊ አስተዋፅኦ እንዳለውም አያይዘው ገልፀዋል።
በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የውጪ ቋንቋዎች ማኔጂንግ ኤዲተርና በተቋሙ ውስጥ በአሁኑ ሰዓት የአብርኆት ቤተ መጻሕፍት የመጽሐፍት አሰባሳቢ ኮሚቴ ሰብሳቢ በመሆን እየተጉ የሚገኙት አቶ ግዛቸው ደርብ ዩኒቨርሲቲው ለአብርሆት ቤተመጻሕፍት ላደረገው የመጻሕፍት አበርክቶ ከልብ አመስግነው፣ ሌሎች ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትም የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲን ፈለግ እንዲከተሉ ጠይቀዋል።
                                     የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት
May be an image of book
Posted in Office of the Communication Affairs, Uncategorized.

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *