ኮትዩ በዩኒቨርሲቲው የሽግግር ሂደት ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ከፍተኛ የምክክር መርሐግብር አካሄደ።

ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ከሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት፣ ከትምህርት ሚኒስቴር፣ ከፕላንና ልማት ሚኒስቴር፣ ከክልል ትምህርት ቢሮዎችና ከሌሎችም ተቋማት የተጋበዙ የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም እውቅ የሃገሪቱ የሥነ ትምህርት ምሁራንን ያሳተፈ፣ በዩኒቨርሲቲው ሁለንተናዊ የሽግግር ሂደት ሰነዶች ላይ በከፍተኛ ደረጃ የሚመክር እና የሃገሪቱን ብቸኛ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ በጠንካራ መሠረት ላይ ለመመስረት ያለመ የውይይት መድረክ ሰኔ 2/2014 ዓ.ም በቢሾፍቱ ከተማ አካሄደ።
የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት የተከበሩ ዶ/ር ብርሃነመስቀል ጠና ለተጋባዥ እንግዶች ባደረጉት የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት፣ ኮተቤ ስፔሻላይዝድ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ እንዲሆን መስከረም 24/2014 ዓ.ም በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ከተወሰነ ጊዜ ጀምሮ፣ የተለያዩ ቴክኒካል እና አብይ ኮሚቴዎች ተዋቅረው ዘርፈ ብዙ ሥራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን ተናግረዋል። መድረኩ ያስፈለገውም ለታላቅ ዓላማ ሲሆን፣ ይህም በተለያዩ ኮሚቴዎች የተዘጋጁ ሰነዶች ላይ ከዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት በማድረግ ሰነዶቹን የበለጠ ለማዳበርና ጠንካራ ሃገራዊ የትምህርት ተቋም መገንባት ነው ብለዋል ዶ/ር ብርሃነመስቀል። ፕሬዝዳንቱ አያይዘውም፣ ይህንን ታላቅ ዓላማ ለማሳካት ተቋሙ በሚያደርገው ጥረት ከፍተኛ እገዛ በማድረግ ላይ የሚገኘውን የትምህርት ሚኒስቴር እና ሌሎች የሥነ ትምህርት ባለሙያዎችን አመስግነዋል።
የውይይት መድረኩን በንግግር እንዲከፍቱ የተጋበዙት የትምህርት ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታ የተከበሩ ዶ/ር ፋንታ ማንደፍሮ በበኩላቸው መድረኩ የተዘጋጀበትን ዋና ዓላማ የሃገሪቱን ቀዳሚ ተግባር በቀዳሚው ተቋም ማስቀመጥ ነው ሲሉ ገልጸውታል። በመቀጠልም፣ ዶ/ር ፋንታ ማንደፍሮ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በርካታ የትምህርት ተቋማትን ብናፈራም፣ ውስን ዘርፎች ላይ አተኩረው ባለመስራታቸው እንደሃገር ዋጋ አስከፍሎናል ብለዋል። ዶ/ር ፋንታ አያይዘውም፣ የሃገራችን ዕድገትና ብልጽግና የሚወሰነው በትምህርት በመሆኑ፣ ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ትምህርትን በማሻሻልና በመምህራን ሥልጠና ላይ ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራ ተቋም እንዲሆን ሁሉም በቅንነት አስተዋጽዖ እንዲያደርግ አሳስበው፤ የትምህርት ሚኒስቴርም በበኩሉ ለኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ሙሉ ድጋፍ እንደሚሰጥና አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ሁሉ አሟጦ አብሮ እንደሚሰራ ለተሳታፊው አረጋግጠዋል።
በመድረኩም የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ Roadmap, Curriculum Development Framework እና Cost Modeling for 2015-19 የሚሉ ሰነዶች በየኮሚቴው ተወካዮች አማካኝነት ቀርበዋል። የመድረኩ ተሳታፊዎችም በቀረቡት ሰነዶች ላይ የተለያዩ ጥያቄዎች፣ አስተያየቶችና ሐሳቦች አቅርበው፣ በዶ/ር ብርሃነመስቀል ጠና እና በዶ/ር ፋንታ ማንደፍሮ አወያይነት ሰፊ፣ በሳልና ገንቢ ውይይት እንዲሁም ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል።
ዶ/ር ብርሃነመስቀል ጠና የውይይት መድረኩን በዘጉበት ንግግራቸው፣ በመድረኩ ጥሩ ግብዓቶች መገኘታቸውን ገልጸው፣ ሰነዶቹ በቀጣይ በቀረቡት ግብዓቶች መሠረት ዳብረው በየደረጃው ለዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ፣ለቦርድና ለሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት እንደሚቀርቡ ተናግረዋል። በመጨረሻም፣ በውይይት መድረኩ በመገኘት ለሃገር የሚጠቅም ተቋም ለመገንባት የሚያግዙ ገንቢ ግብዓቶችን ላቀረቡ ሁሉ በራሳቸውና በዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ስም አመስግነዋል።
                                                              የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት
May be an image of 1 person and standingMay be an image of 1 person and standingMay be an image of 1 person and standingMay be an image of 2 people, people sitting and suitMay be an image of 10 people, people sitting, people standing and indoorMay be an image of 1 person and standingMay be an image of 5 people, people sitting and indoorMay be an image of 10 people, people sitting, people standing and indoorMay be an image of 9 people, people sitting, people standing and indoorMay be an image of 1 person, standing and indoorMay be an image of 1 person, standing and indoorMay be an image of 11 people, people sitting and people standingMay be an image of 10 people, people sitting, people standing and indoorMay be an image of 11 people, people sitting, people standing and indoorMay be an image of 7 people, people sitting, people standing and indoor
Posted in Office of the Communication Affairs.

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *