ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ በተቋማዊ የሽግግር ሰነዶች ላይ ከመምህራን ጋር ውይይት አካሄደ፡፡

ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ በተቋማዊ የሽግግር ሰነዶች ላይ ከመምህራን ጋር ዛሬ 23/12/2014 ዓ.ም. በዋና ግቢ ውይይት አካሄዷል፡፡ የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ብርሃነመስቀል ጠና በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት አብይና ቴክኒካል ኮሚቴ ተዋቅሮ ሰፋ ያለ ጊዜ ተወስዶ ሲዘጋጅ የቆየው የዩኒቨርስቲው ምስረታ ፍኖተ ካርታው እና የካሪኩለም ማዕቀፍ ከመነሻው ጀምሮ ባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ ሁኔታ እንዲሆን ተደርጓል። በዚህም በየደረጃው ያሉ አመራሮች እና የዘርፉ ከፍተኛ ምሁራን፣ የቦርድ አመራሮች ፣ የትምህርት ሚኒስቴር አመራሮች፣ የዩኒቨርሲቲው ካውንስል ወዘተ ተወያይተውበት ግብዓት ሰጥተውበታል።
ፕሬዚዳንቱ አያይዘው እንዳሉት እየተዘጋጀ ያለው ፍኖተ ካርታ እና የሥርዓተ ትምህርት ማዕቀፍ በአጠቃላይ የሀገሪቱን የትምህርት ጥራት ችግር እና ክፍተት ለመሙላት ታሳቢ ያደረገ በመሆኑ ከራሳችን ጀምረን ክፍተቱን የሚያርም ዝግጅት ማድረግ ይጠበቅብናል፤ በመሆኑም የዩኒቨርሲቲው መምህራን ለአዲሱ ተልዕኮአችን ብቁነታቸውን ማረጋገጥ ፤ ራሳቸውን ማዘጋጀት ፤ “ማነው መምህር ?” የሚለውን መመለስ ይጠበቅባቸዋል። ለዚህ መሠረታዊ ጉዳዩ ከቀደመው አስተሳሰብ ወጥቶ በአዲስ እይታ አዲሱን ሀገራዊ ተልዕኮና ኃላፊነት በአዲስ አስተሳሰብ መቀበልና ለዚያ ትግበራ ብቁ ሆነው ለመገኘት የትምህርት ዩኒቨርሲቲዎችን ልምድ ማየትና መረዳት አለብን ብለዋል ።
ለስኬቱም ተቋሙ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ እንደመሆኑ ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች፣ የትምህርት ቢሮዎች ፣ የፌዴራል እና የክልል የሥልጠና ተቋማት ቀጥተኛ ባለድርሻዎቻችን ናቸው። ከዚህም አንፃር ከባለድርሻ አካላቱ እንዲሁም ከዘርፉ ምሁራን ጋር ቅንጅት በመፍጠር የተለያዩ ሀገራትን ተሞክሮንም በመቀመር ሰነዶቹን የበለጠ ማዳበር እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።
የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ጊ/ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሽመልስ ዘውዴ እንደተናገሩትም፣ ዩኒቨርሲቲው አዘጋጅቶ በተለያዩ መድረኮች ለባለድርሻ አካላት ለውይይት ካቀረባቸው ሰነዶች መካከል የተቋሙ የሽግግር ፍኖተ ካርታ እና የሥርዓተ ትምህርት ማዕቀፍ ላይ የዩኒቨርሲቲው መምህራን እንዲወያዩባቸው መድረኩ የተዘጋጀው ከመስከረም 2015 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ትግበራ የሚገባ በመሆኑ መምህራኑ በቂ ግንዛቤ በመጨበጥ ቅድመ ዝግጅት እንዲያደርጉ ለማስቻል እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
ዶ/ር ፈቀደ ቱሊ ለውይይቱ የመነሻ ሀሳብ ባቀረቡበት ወቅት እንደተናገሩት፤ የተቋሙ የሽግግር ፍኖተ ካርታ ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ብቸኛው የሀገሪቱ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ እንዲሆን በአዋጅ ከተወሰነበት ጊዜ ጅምሮ በተሰጠው ኃላፊነት መሠረት ሰነዱ የትምህርት ጥራት ችግርን በሚፈታ እና ሁለንተናዊ የትምህርት አካሄድን በሚያግዝ መልኩ መዘጋጀቱን ለውይይቱ ተሳታፊዎች አብራርተዋል፡፡ ዶ/ር ኤፍሬም ተክሌ በበኩላቸው የሥርዓተ ትምህርት ማዕቀፉ የዩኒቨርሲቲውን አጠቃላይ የመማር ማስተማር ሂደት የሚመራ ሲሆን፣ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር መዘጋጀቱን እና በተለያዩ ባለድርሻ አካለት በተለያዩ ጊዜያት ውይይት የተደረገበት መሆኑን አመልክተዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው መምህራንም በበኩላቸው በቀሩት የዩኒቨርሲቲው ተልዕኮ፤ የትምህርት መርሀግብሮችና ስያሜዎቻቸው እንዲሁም በተማሪዎች አቀባበል ሁኔታዎች ላይ በማተኮር ሰፊ ገንቢ ሀሳቦችን በማንሳት በውይይቱ ላይ ንቁ ተሳትፎ አድርገዋል፡፡
                                የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት
May be an image of 3 people, people sitting and indoorMay be an image of 7 people and people sitting
Posted in Office of the Communication Affairs, Uncategorized.

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *