“ለኢትዮጵያ ልዕልና የምሁራን ሚና” በሚል መሪ ቃል የምሁራን መድረክ በኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ እና በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ትብብር መዘጋጀቱ ተገለፀ፡፡

የሁለቱም ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶች በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደገለፁት፣ “ለኢትዮጵያ ልዕልና የምሁራን ሚና” በሚል መሪ ቃል የፊታችን ሰኞ ህዳር 26 ቀን 2015 ዓ.ም በኃይሌ ግራንድ ሆቴል የሚካሄደው የምሁራን መድረክ ቅድመ ዝግጅቱ ተጠናቋል፡፡
የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ብርሃነመስቀል ጠና እንዳሉት ይህ መድረክ ምሁራን በነፃነት የሚወያዩበት፣ የሃሳብ ልዕልና የሚፀባረቅበት፣ ለወቅታዊ ችግሮቻችን የሚበጁ ምክረ-ሃሳቦችም የሚቀርቡበት ይሆናል፡፡ በዚህ የምሁራን መድረክ ላይ ከ300 በላይ የሚሆኑ በዩኒቨርሲቲዎችና በተለያዩ የምርምር ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ ምሁራን እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት የሚያሳተፉ ሲሆን፣ ሀገራዊ እና ዓለማቀፋዊ ጉዳዮችን የሚያስቃኙ ሁለት የውይይት መነሻ ጽሑፎች ቀርበው ምሁራዊ ውይይት እንደሚካሄድባቸውም ዶክተር ብርሃነመስቀል ጠና ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ደረጀ እንግዳ የምሁራንን አቅም የመጠቀም ውስንነት እንደነበር ጠቅሰው ከአሁን በኋላ ግን የምሁራን ተሳትፎ ለማሳደግ ተከታታይ ውይይቶች እንደሚዘጋጁ አመልክተዋል፡፡
ተጋባዥ ምሁራን በዚህ መድረክ ላይ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ሀገርን የሚያሻግር ሐሳብ በማቅረብ የዜግነት ድርሻቸውን እንዲወጡ ዶክተር ብርሃነመስቀል ጠና እና ዶክተር ደረጀ እንግዳ ጠይቀዋል፡፡
                               ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት
Posted in Office of the Communication Affairs, Uncategorized.

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *