ኮ.ት.ዩ. ሀገሪቱ የምትፈልጋቸውን የትምህርት ባለሙያዎች በጥራት እንዲያሰለጥን ትልቅ ኃላፊነት የተሰጠው ዩኒቨርሲቲ መሆኑ ተገለፀ፡፡

በኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ኃብት ልማት፣ ሥራ ሥምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ዩኒቨርሲቲውን በጎበኙበት ወቅት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ እንደገለፁት፣ ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ (ኮ.ት.ዩ.) ሀገሪቱ የምትፈልጋቸውን የትምህርት ባለሙያዎች በጥራት እንዲያሰለጥን ትልቅ ኃላፊነት የተሰጠው ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡
ሀገሪቱ ያለባትን የትምህርት ጥራት ችግር መፍታት ብቃት ያላቸውን የትምህርት ባለሙያዎችን እንዲያፈራ ትልቅ ኃላፊነት የተሰጠውን ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የሚገኝበትን አቋም ለመገምገም የመስክ ምልከታ ያካሄደ መሆኑን የጠቀሱት ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ፣ ቋሚው የኮሚቴ አባላት ለመስክ ምልከታው ትልቅ ቦታ እንዳላቸውም አመልክተዋል፡፡
የመስክ ምልከታውን ትኩረት አስመልክቶ በተካሄደው ውይይት ወቅት የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ብርሃነመስቀል ጠና እንዳሉት፣ ዩኒቨርሲቲው በነበረው የስያሜ፣ ተልዕኮ እና የአደረጃጀት ለውጥ፣ የቦታ ጥበት፣ በበጀት እና በመሠረተ ልማት ረገድ የተለያዩ ችግሮች ቢኖሩበትም ውጤታማ የሆኑ ልዩ ልዩ ሀገራዊ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡ በተለይም ከመስከረም 24/2014 ዓ.ም ጀምሮ ተቋሙ የተሰጠውን አዲስን ተልዕኮ በብቃት እንዲወጣ የሚያስችሉት ፍኖተ ካርታ እና ሥርዓተ ትምህርት የማዘጋጀት፣ የውጭ ሀገር ተሞክሮ የመቀመር፣ በውጭ እና በሀገር ውስጥ ዕውቅ ምሁራን የማስገምገም፣ ከተለያዩ ባለከድርሻ አካላት ጋር ውይይት የማካሄድ፣ ተቋሙን በአዲስ መልክ የማደራጀት እና የግንባታ ስራዎችን ውጤታማ በሆነ መልኩ የተከናወኑ መሆኑን የገለፁት ዶ/ር ብርሃነመስቀል፤ አሁንም ቀሪ ስራዎች በትጋት እየተሰሩ ስለመሆናቸው ተናግራዋል፡፡
ከመነሻ ውይይቱም በኋላ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ በሚገኙ የቤተመጻሕፍት፣ የተማሪዎች መኝታ ክፍል እና የመመገቢያ አዳራሽ፣ ክሊኒክ፣ የመማሪያ ክፍሎች እንዲሁም ነባር እና እየተሰሩ ያሉ የህንፃ ግንባታዎች በመስክ ምልከታው የተጎበኙ ሲሆን ከጉብኝቱ በኋላም ከዩኒቨርሲቲው መምህራን እና የአስተዳደር ሰራተኞች ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡
በተደረገው ውይይትም ወቅት የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ መሠረተ ልማትና ለመማር ማስተማሩ የሚያስፈልጉ ግብዓቶች በተፈለገው ደረጃ አለመኖር እንደ ችግር የገለፁ ሲሆን፣ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ በሰጡት ምላሽም ዩኒቨርሲቲው ትልቅ የሰው ሃብት ስላለው ተስፋ የሚጣልበት በመሆኑ የተዘረዘሩት የቦታ ጥበት፣ የበጀት፣ የመሠረተ ልማት እንዲሁም የመምህራን ጥቅማ-ጥቅም እና የደመወዝ ችግሮች በሂደት እንዲፈቱ ቋሚ ኮሚቴው ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር ደረጃ በደረጃ እንደሚወያይ፣ ችግሮቹም እንደሚፈቱ ጠቅሰው እስከዚያው ድረስ ግን የመማር ማስተማሩ ሂደት በሰላማዊ መንገድ እንዲቀጥል መምህራን የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡
                                            የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት
May be an image of 7 people, people standing, people sitting and indoor
Posted in Office of the Communication Affairs, Uncategorized.

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *