ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎቹን በደማቅ ሁኔታ አስመረቀ፡፡

ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ (ኮሜዩ) በ2013 ዓ.ም የትምህርት ዘመን በቅደመ-ምረቃና በድህረ-ምረቃ በቀንና በማታ መርሀ-ግብሮች ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ 2526 ተማሪዎችን ዛሬ ጥቅምት 6 ቀን 2014 ዓ.ም በደማቅ ሁኔታ አስመርቋል፡፡
የኮሜዩ ፕሬዝዳንት የተከበሩ ዶ/ር ብርሃነመስቀል ጠና በበኩላቸው የኮቭድ-19 ወረርሽኝ ጫናን እና በሀገር ሉዓላዊነት ላይ የተደቀኑ ተግዳሮቶችን ሁሉ ተቋቁማችሁ ለዛሬ ምረቃ የበቃችሁ እንኳን አደረሳችሁ ያሉ ሲሆን ዛሬ ሀገራችን በፈተና ውስጥ ባለችበት የተመረቃችሁ ምሩቃን ሀገራችሁን የምትከላከሉ፣ ፍትህን የምታረጋግጡ ።፣ ሌብነትን የምትዋጉ ፣ ህብረ ብሔራዊ ወንድማማችነትን የምታጎለብቱ፣ ለሀገራችሁ በየደረሳችሁበት አምባሳደሮች እንድትሆኑ ።፣ በየተመረቃችሁበትም ሙያችሁ ለሀገራችሁ ለብልጽግናዋ የድርሻችሁን የምትወጡ እንድትሆኑ ሲሉ የአደራ መልዕክታቸው አስተላልፈዋል።
ፕሬዚዳንቱ አያይዘውም ዩኒቨርሲቲው በትምህርት ረገድ ያለውን ደማቅ ታሪካዊ አሻራውን እንዲያስቀጥል “ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ” ሆኖ በአዋጅ በመቋቋሙ መላው የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብን እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
የዩኒቨርሲቲው ቦርድ ሰብሳቢ የተከበሩ የክብር ዶ/ር አባዱላ ገመዳ ባደረጉት ንግግር የዕለቱ ምሩቃን እንደሀገርም ሆነ እንደግለሰብ ባጋጠማቸው ተግዳሮቶች ሳይገቱ በአስቸጋሪ ወቅት ሁሉንም ጫና ተቋቁመው ለመመረቅ በመብቃታቸው እንኳን ደስ አላችሁ ካሉ በኋላ በቀጣይም ምሩቃኑ ተግዳሮቶችን እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም የልማትና የሰላም ጅምር ሥራዎችን በማስቀጠል ረገድ ተስፋ የተጣለባቸው መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡ ቀጥሎም ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ አሁን ለደረሰበት ደረጃ ላደረሱት መላው የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብና አመራሮች ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በሌላ በኩል የኢፌዲሪ የውጪ ጉዳዮች ሚንስቴር ቃለ-አቀባይ የተከበሩ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ለተመራቂዎቹ ባስተላለፉት መልዕክታቸው ሁሉም በሙያው ቋንቋ፣ ሀይማኖትና ዘር ሳይለው የሀገሩ አምባሳደር ስለሆነ ምሩቃኑ ልዩነትንና ብዝሀነትን እንደ ህብር ጌጥ በመውሰድ የሀገራቸው አምባሳደሮች መሆናቸውን ተገንዝበው በአንድነት ለሀገር ግንባታና ለሰላም መስፈን መስራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡
በመጨረሻም ዩኒቨርሲቲው በትምህርታቸው ብልጫ ላመጡ ተማሪዎች ልዩ ልዩ ሽልማቶችን ከመስጠት ባሻገር ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ የአመራርነት እርከን ደረጃ አስተዋፅኦ ላበረከቱት ዶ/ር ደመወዝ አድማሱ የዕውቅና ሽልማት ከምስጋና ጋር ሰጥቷል፡፡
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር
Posted in Uncategorized.

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *