ታላቁ የህዳሴ ግድባችን የድህነት ማሸነፊያ ተስፋችን መሆኑ ተገለጸ

ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ፕሮጀከት ጽ/ቤት ጋር በመተባበር በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ወቅታዊ ግንዛቤ ለመፍጠር ያለመ የውይይት መርሐ-ግብር በ26/06/2014 ዓ.ም በዩኒቨርሲቲው ዋና ግቢ አስተናግዷል።
ውይይቱ በተጀመረበት ወቅት የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያሰሙት የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት የተከበሩ ዶክተር ብርሃነመስቀል ጠና፣ የህዳሴው ግድብ የድህነት ማሸነፊያ ተስፋችን መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በመቀጠልም ፕሬዝዳንቱ ግድቡ የይቻላል አቅም መገንቢያችን በመሆኑ ወጣቱ ትውልድ የህዳሴው ግድብ አምባሳደሮች በመሆን ለዓለም ህዝብ ስለህዳሴው ግድብ መመስከር እና በየዕለቱም መናገር ብሎም በቀጣይነት ድጋፉን ማጠናከር ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ከሚመገቡት ምግብ በመቀነስ ለህዳሴው ግድብ ስኬት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ሲያበረክቱ መቆየታቸውን ያስታወሱት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት፣ በቀጣይም ከድህነት እና ከጨለማ ውስጥ የመውጣት አስተሳሰብ በማጎልበት በእውቀታችን፣ በገንዘባችንና በጉልበታችን አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የትምህርት ሚኒስቴር ተወካይ የሆኑት ዶክተር ታምራት ይገዙ በበኩላቸው ትምህርት ከድህነት ለመውጣት ከፍተኛ ሚና ያለው በመሆኑ መንግሥት ለትምህርት ልዩ ትኩረት በመስጠት እየሰራ የሚገኝ መሆኑን ጠቅሰው፣ በእውቀት የታነፀ እና ሀገርን ከድህነት ለማውጣት ቁርጠኛ የሆነ ትውልድ ለማፍራት በተለይ የወጣቱ ትውልድ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ወጣቱ ትውልድ ባለፉት ዓመታት ለህዳሴው ግድብ መሳካት ቦንድ በመግዛት ያሳየው የነቃ ተሳትፎ ለሀገሩ እድገት የሚቆረቆር ዜጋ እያፈራን ስለመሆኑ ምስክር ነው በማለትም ተናግረዋል፡፡
በዕለቱም ለውይይት መነሻ የሚሆኑ ሦስት ጽሑፎች ቀርበው በተማሪዎቹ ውይይት የተካሄደባቸው ሲሆን፣ ተማሪዎች በህዳሴው ግድብ ዙሪያ እውቀት፣ አስተሳሰብና አመለካከትን በአግባቡ በመቅረፅ እና በተለያዩ የማህበራዊ ትስስር ገጾች በማስረዳትና በማስተዋወቅ፣ አፍራሽ አመለካከቶችን በመመከት እንዲሁም ትክክለኛውን መረጃ በመስጠት የአምባሳደርነት ሚናቸውን መወጣት አለባቸው ተብሏል፡፡ ተማሪዎችም በበኩላቸው የራሳቸውን ሚና እንደሚወጡ ገልጸዋል፡፡
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ፕሮጀከት ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አረጋዊ በርሄ ከዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጋር የተደረገው ውይይት ውጤታማ እንደነበር ጠቅሰው ተማሪዎችም ሀገሪቱን ከጨለማ ወደ ብርሃን ለማሸጋገር በሚደረገው ጥረት የእስካሁኑን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል፡፡
                               የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳሬክቶሬት
Posted in Office of the Communication Affairs, Uncategorized.

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *