ዩኒቨርሲቲው ከቀጣዩ ዓመት ጀምሮ ተማሪዎችን በውድድር ተቀብሎ ማስተማር ሊጀምር ነው::

ሚያዝያ 11/2014 (ዋልታ) ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ከ2015 የትምህርት ዘመን ጀምሮ ተማሪዎችን በውድድር ተቀብሎ ማስተማር ሊጀምር መሆኑን አስታወቀ፡፡

የቀድሞው ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ከወራት በፊት በአዋጅ ወደ ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ መቀየሩ ይታወሳል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ብርሀነመስቀል ጠና (ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ በኢትዮጵያ ከዚህ በፊት የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ባለመኖሩ ለትምህርት ጥራት መጓደል አንድ ምክንያት ሆኖ መቆየቱን ጠቅሰው ችግሩን ለማቃለል ሲባል ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ እውን መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም በተለያዩ ችግሮች እየተፈተነ የሚገኘውን የኢትዮጵያ የትምህርት ዘርፍ ለማከም ከወራት በፊት ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ትልቅ ኃላፊነት ወስዶ ወደ ሥራ ገብቷል ብለዋል።

የትምህርት ዩኒቨርሲቲው የመምህራንን ትምህርት ዋነኛ ምሰሶ በማድረግ የትምህርት አመራሮች፣ ተመራማሪዎች፣ አማካሪዎችና ፖሊሲ አውጪዎችን ማፍራት ላይ አተኩሮ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ መንገድና መዳረሻ ምን እንደሆነ የሚያሳይ ፍኖተ ካርታ በዝግጅት ላይ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

በዘንድሮው የትምህርት ዘመን ከነባር የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች በተጨማሪ በትምህርት ሚኒስቴር የሚመደቡለትን ተማሪዎች ተቀብሎ ለማስተማር መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡

ከቀጣዩ የትምህርት ዘመን ጀምሮ ግን ዩኒቨርሲቲው ዓላማውን ለማሳካት ያስችለው ዘንድ ተማሪዎችን በፈተና አወዳድሮ በመቀበል ማስተማር ይጀምራል ብለዋል።

Source: Walta TV

Posted in Uncategorized.

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *