የኮትዩ አስተዳደር ካውንስል የዩኒቨርሲቲውን አዲስ ሎጎ በአብላጫ ድምፅ መረጠ።

የቀድሞው ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ በአዋጅ ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ተብሎ መሰየሙን ተከትሎ፣ የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ካውንስል በሁለት ባለሙያዎች የተዘጋጁ ዓርማዎች ወይም ሎጎዎች ላይ ሚያዝያ 19 ቀን 2014 ዓ.ም ውይይት ከአካሄደ በኃላ፣ የዩኒቨርሲቲውን አዲሱን ተልዕኮ እና አወቃቀር በተሻለ ደረጃ ያንጸባርቃል ያለውን ሎጎ በአብላጫ ድምፅ መርጧል።
የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ብርሃነመስቀል ጠና በስነስርዓቱ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ከዩኒቨርሲቲው የአዲሱ ስያሜ ለውጥ ጋር ተያይዞ አዲስ ዓርማ (ሎጎ) በማስፈለጉ፣ ልምድ ያላቸውን ሁለት የዘርፉ ባለሙያዎች ተጋብዞ የዓርማው ስራ መከናወናቸውን ገልፀው፣ ስራውም የተለያዩ የዝግጅት ሂደቶችን ካለፈ በኋላ፣ በዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ካውንስል አባላት ውይይት እና ትችት እንዲካሄድበት መቅረቡን ተናግረዋል።
እንደ ዶ/ር ብርሃነመስቀል ገለፃ፣ በዚህና በቀጣይ ዓመታት የዩኒቨርሲቲያችን አዲሱ ስያሜና ተልዕኮው ላይ አተኩረን መሥራት እንደሚጠበቅብንና የመምህርነትን ሙያ ተማሪዎች ፈልገው የሚገቡበት ብቻ የማድረግ ኃላፊነት የሁሉም የዩኒቨርሲቲው ሠራተኞች መሆኑን በአጽንዖት ተናግረዋል።
በቅርቡ ህይወታቸው ያለፈው የአርትና ሚዩዚክ የት/ት ክፍል ባልደረባ በነበሩት በአቶ ታደሰ የተሰሩ አራት ሎጎዎች በልጃቸው በወ/ሮ ፌቨን ታደሰ በኩል፣ በአርክቴክቸር ምህንድስና ት/ት ክፍል መምህሩ በአቶ ፍሬው ዘሪሁን ደግሞ አምስት የተለያዩ ስራዎች የቀረቡ ሲሆን፣ በመጀመሪያው ዙር በድምፅ ብልጫ ከሁለቱ ባለሙያዎች ስራዎች አንድ አንድ ተመረጡ። በመቀጠልም፣ ከሁለቱ ሎጎዎች አንዱን ለመምረጥ በተደረገው የድምፅ አሰጣጥ ሂደት የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ካውንስል አባላት በአቶ ፍሬው ዘሪሁን የተሰራውን ሎጎ በአብላጫ ድምፅ አሳልፏል።
በአብላጫ ድምፅ የተመረጠው ስራ በዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ካውንስል አባላት የቀረቡትን ግብዓቶች በማካተት፣ የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ አዲሱ ሎጎ ሆኖ በቅርቡ እንደሚጸድቅ ይጠበቃል።
ከዚሁ ጋር አያይዘው ፕሬዝዳንቱ እንደገለፁት፣ ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የሚገቡ ተማሪዎችን ዩኒቨርሲቲው የሚቀበለው በፈተና በመለየት በመሆኑ፣ በትምህርት ጥራት ዳይሬክቶሬት ስር የመግቢያ ፈተና ማስተባበሪያ ቢሮ ተደራጅቶ የዝግጅት ሥራ እየተሰራ እንደሆነ ገልጸዋል፤ በመቀጠልም ዩኒቨርሲቲው በአዲሱ ስያሜው አዲስ ተማሪዎችን ለመቀበል የተለያዩ ቅድመ ዝግጅቶችን አጠናቆ፣ የተማሪዎችን መምጣት በመጠባበቅ ላይ መሆኑን እና የሚመለከታቸው የስራ ክፍሎችም ቀሪ ተግባራትን ማከናወን እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት
 
Posted in Office of the Communication Affairs, Uncategorized.

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *