10ኛው የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና የፈጠራ ውጤት ቀን በኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ በደማቅ ሁኔታ ተከበረ።

ሚያዚያ 28/2014 ዓ.ም
ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ 10ኛውን የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና የፈጠራ ውጤት ቀንን ባከበረበት ወቅት የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ኢንጂነሪንግና ማቲማቲክስ ትምህርት (STEM Education) ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት ዶክተር ቴዎድሮስ ሙሉጌታ፣ የበዓሉ ዋና ዓላማ 21ኛውን ክፍለ ዘመን የሚመጥን የሰው ኃይል በማፍራት የህብረተሰቡን ችግሮች በዘለቄታዊ ሁኔታ የሚቀርፉ የሳይንስ ውጤቶችን በተሻለ መንገድ ማቅረብ እንደሆነ ገልጸዋል። ዕለቱን በተማሪዎች መካከል ውድድር በመፍጠር ማክበርም ይህንን ዓላማ ከማሳኪያ መንገዶች አንዱ እና ዋነኛው መሆኑን አስገንዝበዋል።
በዚህም መሠረት በየካ ክፍለ ከተማ የሚገኙ ትምህርት ቤቶችን በማሳተፍ የፈጠራ ውጤታቸውን እንዲያቀርቡ በማድረግ፣ ዕለቱን በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ማክበር እንደተቻለም አመልክተዋል። በዕለቱም በክፍለ ከተማው ከሚገኙ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም ከሳይንስ ሼርድ ካምፓስ 39 ፕሮጀክቶች በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ፣ በፈጠራ እና በአይ.ሲ.ቲ ዘርፍ ቀርበው የተወዳደሩ ሲሆን፣ ለአሸናፊዎችም ሽልማት ተሰጥቷል።
በተማሪዎች የቀረቡት ፕሮጀክቶች ተስፋ ሰጪ በመሆናቸው ፕሮጀክቶቹ ጥቅም ላይ የሚውሉበትን መንገድ ማመቻቸት ከዩኒቨርሲቲው እና ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከታቸው አካላት የሚጠበቅ መሆኑንም ዶክተር ቴዎድሮስ ሙሉጌታ አስገንዝበዋል።
                                                          የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት
Posted in Office of the Communication Affairs, Uncategorized.

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *