የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ፋካልቲ የጀመረው ዕውቀትን የማጋራት መርሐ ግብር ለአካዳሚክ እውቀት ዕድገት ጠቃሚ በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተገለፀ።

ሚያዝያ 25/2014 ዓ.ም
የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ፋካልቲ ዕውቀትን የማጋራት መርሐ ግብሩን በ25/08/2014 ዓ.ም ባካሄደበት ወቅት የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ጊ/ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶክተር ሽመልስ ዘውዴ ባሰሙት የመክፈቻ ንግግር፣ ፋካልቲው የጀመረው እውቀትን የማጋራት መርሐ ግብር ለአካዳሚክ እውቀት ዕድገት ጠቃሚ በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል። የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ፋካልቲ እንቅስቃሴውን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሰፋ እና የተለያዩ ተቋማትን እያሳተፈ መምጣቱን የጠቀሱት ዶክተር ሽመልስ፣ ለአካዳሚክ ዕውቀት እድገት በየጊዜው የሚደረግ አካዳሚያዊ የሆነ የውይይት መነሻ ሐሳብ መኖር ወሳኝ በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት እና የዕለቱ ዕውቀትን የማጋራት መርሐ ግብርም ስኬታማ እንዲሆን ያላቸውን መልካም ምኞት ገልፀዋል።
የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ፋካልቲ ዲን ዶ/ር ኃይለሚካኤል ሙሌ በበኩላቸው፣ ፋካልቲው በዕቅዱ መሠረት የምርምር ጉባኤ፣ የእውቀት ማጋራት መርሐ ግብሮችን፣ የቢዝነስ ዜና መጽሔት እንዲሁም ሌሎች ተመሳሳይ ተግባራትን በመምህራን እና በተማሪዎች አማካኝነት እያከናወነ ነው ብለዋል። የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ፋካልቲ ፈር ቀዳጅ በመሆን የጀመራቸውን ልዩ ልዩ ተግባራትንም አጠናክሮ ይቀጥላል ያሉት ዲኑ፣ የምርምር ሥራ ውጤት ለአካዳሚክ ማህበረሰብ ቀርቦ ውይይት ከተደረገበት በኋላ የህብረተሰቡን ችግር መፍታት እና በጥቅም ላይ መዋል እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የፋካልቲው መምህር የሆኑት ዶክተር ያኪን አሊ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ የዋጋ ንረት በህብረተሰቡ ላይ ከፍተኛ ጫና እየፈጠረ በመሆኑ መፍትሔ የሚያሻው መሆኑን የገለፁ ሲሆን፣ መምህር ይልቃል ዋሴ ደግሞ የሀገሪቱ መዋቅራዊ ለውጥ ወደ አገልግሎት አሰጣጥ ያዘመመ በመሆኑ ከሥራ ዕድል ፈጠራ አንፃር ውስንነት ስለሚኖረው የግብርና ምርት እና ምርታማነትን በመጨመር አገልግሎትን ማስፋት እና ወደ ፋብሪካ እና ኢንዱስትሪ መቀየር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
በቀረቡት ሁለት ጥናታዊ ጽሑፎች ላይ ውይይት የተደረገ ሲሆን፣ የውይይቱ መርሐ ግብር ሲጠናቀቅ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ፋካልቲ ዲን ዶ/ር ኃይለሚካኤል ሙሌ ፋካልቲው በቀጣይ ሀገር ዓቀፍ መድረክ ለማዘጋጀት ማቀዱንም አመልክተዋል።
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት
Posted in Uncategorized.

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *