የቀድሞ የኮተቤ ትምህርት ኮሌጅ ተማሪ ዶ/ር አብረሃም አለሙ ለኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ መጻሕፍትን ለገሱ፡፡

የቀድሞ የኮተቤ ትምህርት ኮሌጅ ተማሪ እና ከቅርብ ዓመታት ወዲህ መኖሪያቸውን በውጭ ሀገር ያደረጉት ዶ/ር አብርሃም አለሙ ለኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ዛሬ ነሀሴ 12/2014 ዓ.ም 709 መጻሕፍትን ለግሰዋል፡፡
የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ብርሃነመስቀል ጠና በመጻሕፍት ርክክብ መርሀግብሩ ላይ እንደገለፁት፣ ዶክተር አብርሃም አለሙ ለዩኒቨርሲቲው ያበረከቱት መጻሕፍት ለትውልድ እና ለሀገር የሚጠቅሙ በመሆናቸው ትልቅ ግምት የሚሰጣቸው ናቸው፡፡ በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በተሰማሩበት መስክ የሙያ እና የቁሳቁስ ድጋፍ ቢያደርጉ፣ ይህንንም በጎ አድራጎት አንዱ ለሌላው ቢያስተዋውቅ እና አንድ ላይ ብናብር ሀገራችን በቅርብ ጊዜ ውስጥ ወደተሻለ ደረጃ ልናሸጋግራት ይቻላል ያሉት ዶ/ር ብርሃነመስቀል ጠና፣ ዩኒቨርሲቲው ከዩኒቨርስቲው የዕውቀት ማዕድ ተቋዳሾች ዶ/ር አብርሃምን ሁሌም እንደሚያስታውስ እና እርሳቸውም ሌሎችንም ሀገር ወዳድ ዜጎቻችንን በማስተባበር በቀጣይም ዩኒቨርስቲውን የመደገፍ ጥረታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አድርገውላቸዋል።
በሥነስርዓቱ ላይም ዶክተር አብርሃም አለሙ እንደተናገሩት በ1974ዓ.ም ሰኔ 29 ቀን ከኮተቤ መምህራን ኮሌጅ በዲፕሎማ መርሐግብር መመረቃቸውን አስታውሰው፣ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በመምህርነት እያገለገሉ መሆናቸውን በማውሳት የዛሬ መሠረታቸው ለሆነው ኮትዩ ያበረከቱአቸውን መጻሕፍት በነዚሁ የአገልግሎት ዘመናቸው ከሀገር ውስጥ እንዲሁም ለዶክትሬት ዲግሪ ትምህርት ወደ ሆላንድ በሄዱበት ጊዜ ከውጭ ሀገር የገዟቸውና ያሠባሠቧቸው መሆናቸውን አስታውሰዋል፡፡
መጻሕፍቱ በኢትዮጵያ ስነጽሑፍ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው ድርሰት የሆነውን ጦቢያ ጨምሮ በስነጽሑፍ፣ በቋንቋ፣ በፎክሎር ንድፈ ሐሳብ፣ በአንትሮፖሎጂ፣ በታሪክ እና በሌሎች የሶሻል ሳይንስ የትምህርት መስኮች ላይ ያተኮሩ መሆናቸውን የጠቀሱት ዶ/ር አብርሃም አለሙ፣ “ለዓመታት ያህል አብረውኝ የቆዩትን መጻሕፍት ለተማርኩበት ለቀድሞው የኮተቤ ትምህርት ኮሌጅ ለአሁኑ ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ በመስጠቴ ታላቅ ደስታ ይሰመኛል” ብለዋል፡፡ መጻሕፍቱን ለመረከብ የዩኒቨርሲተው ኃላፊዎች ላደረጉት ትብብርና ቤተሰባዊ አቀባበል አመስግነዋል፡፡
በመጨረሻም ዶ/ር ብርሃነመስቀል ጠና እና ዶ/ር አብርሃም አለሙ በጋራ በመሆን መጻሕፍቱን ለኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ቤተመጻሕፍት እና ዶክመንቴሽን ዳይሬክተር ለሆኑት ለአቶ ገብረመስቀል ግርማ ያስረከቡ ሲሆን፣ ዶ/ር አብርሃም አለሙ ላበረከቱት አስተዋፅዖም በኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ብርሃነመስቀል ጠና አማካኝነት የእውቅና የምስክር ወረቀት የተሰጣቸው መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል፡፡
                                 የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት
May be an image of 10 people and people standing
Posted in Office of the Communication Affairs.

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *