በላቴክስ ሶፍትዌር አጠቃቀም ላይ ያተኮረ ሥልጠና ለመምህራን ተሰጠ።

 

ለጥናት እና ምርምር አጋዥ በሆነው ላቴክስ (Latex) የመተግበሪያ ሶፍትዌር አጠቃቀም ዙሪያ ለኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ መምህራን በፊዚክስ ላብራቶሪ ሚያዝያ 20 ቀን 2014 ዓ.ም ሥልጠና ተሰጥቷል።

ሥልጠናውን ለመምህራኑ የሰጡት ዶ/ር ደረሰ ተርፋ ሲሆኑ፣ ሥልጠናው በተካሄደበት ወቅት እንደገለጹት፣ ለኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ መምህራን የተሰጠው ይህ ሥልጠና፣ ለጥናት እና ምርምር፣ መጽሐፍ ለማዘጋጀት፣ ሪፖርት ለመፃፍ እና ለማቅረብ አጋዥ መሆኑን ተናግረዋል።

ምንም እንኳን ሥልጠናው በመጀመሪያ ዙር ለሳይንስ መምህራን ቢዘጋጅም፣ በቀጣይ ለሌሎች የዩኒቨርሲቲው መምህራን ደረጃ በደረጃ የሚሰጥ መሆኑን ዶ/ር ደረሰ ጠቁመዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት

 
 
 
 

የኮትዩ አስተዳደር ካውንስል የዩኒቨርሲቲውን አዲስ ሎጎ በአብላጫ ድምፅ መረጠ።

የቀድሞው ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ በአዋጅ ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ተብሎ መሰየሙን ተከትሎ፣ የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ካውንስል በሁለት ባለሙያዎች የተዘጋጁ ዓርማዎች ወይም ሎጎዎች ላይ ሚያዝያ 19 ቀን 2014 ዓ.ም ውይይት ከአካሄደ በኃላ፣ የዩኒቨርሲቲውን አዲሱን ተልዕኮ እና አወቃቀር በተሻለ ደረጃ ያንጸባርቃል ያለውን ሎጎ በአብላጫ ድምፅ መርጧል።
የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ብርሃነመስቀል ጠና በስነስርዓቱ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ከዩኒቨርሲቲው የአዲሱ ስያሜ ለውጥ ጋር ተያይዞ አዲስ ዓርማ (ሎጎ) በማስፈለጉ፣ ልምድ ያላቸውን ሁለት የዘርፉ ባለሙያዎች ተጋብዞ የዓርማው ስራ መከናወናቸውን ገልፀው፣ ስራውም የተለያዩ የዝግጅት ሂደቶችን ካለፈ በኋላ፣ በዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ካውንስል አባላት ውይይት እና ትችት እንዲካሄድበት መቅረቡን ተናግረዋል።
እንደ ዶ/ር ብርሃነመስቀል ገለፃ፣ በዚህና በቀጣይ ዓመታት የዩኒቨርሲቲያችን አዲሱ ስያሜና ተልዕኮው ላይ አተኩረን መሥራት እንደሚጠበቅብንና የመምህርነትን ሙያ ተማሪዎች ፈልገው የሚገቡበት ብቻ የማድረግ ኃላፊነት የሁሉም የዩኒቨርሲቲው ሠራተኞች መሆኑን በአጽንዖት ተናግረዋል።
በቅርቡ ህይወታቸው ያለፈው የአርትና ሚዩዚክ የት/ት ክፍል ባልደረባ በነበሩት በአቶ ታደሰ የተሰሩ አራት ሎጎዎች በልጃቸው በወ/ሮ ፌቨን ታደሰ በኩል፣ በአርክቴክቸር ምህንድስና ት/ት ክፍል መምህሩ በአቶ ፍሬው ዘሪሁን ደግሞ አምስት የተለያዩ ስራዎች የቀረቡ ሲሆን፣ በመጀመሪያው ዙር በድምፅ ብልጫ ከሁለቱ ባለሙያዎች ስራዎች አንድ አንድ ተመረጡ። በመቀጠልም፣ ከሁለቱ ሎጎዎች አንዱን ለመምረጥ በተደረገው የድምፅ አሰጣጥ ሂደት የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ካውንስል አባላት በአቶ ፍሬው ዘሪሁን የተሰራውን ሎጎ በአብላጫ ድምፅ አሳልፏል።
በአብላጫ ድምፅ የተመረጠው ስራ በዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ካውንስል አባላት የቀረቡትን ግብዓቶች በማካተት፣ የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ አዲሱ ሎጎ ሆኖ በቅርቡ እንደሚጸድቅ ይጠበቃል።
ከዚሁ ጋር አያይዘው ፕሬዝዳንቱ እንደገለፁት፣ ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የሚገቡ ተማሪዎችን ዩኒቨርሲቲው የሚቀበለው በፈተና በመለየት በመሆኑ፣ በትምህርት ጥራት ዳይሬክቶሬት ስር የመግቢያ ፈተና ማስተባበሪያ ቢሮ ተደራጅቶ የዝግጅት ሥራ እየተሰራ እንደሆነ ገልጸዋል፤ በመቀጠልም ዩኒቨርሲቲው በአዲሱ ስያሜው አዲስ ተማሪዎችን ለመቀበል የተለያዩ ቅድመ ዝግጅቶችን አጠናቆ፣ የተማሪዎችን መምጣት በመጠባበቅ ላይ መሆኑን እና የሚመለከታቸው የስራ ክፍሎችም ቀሪ ተግባራትን ማከናወን እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት
 

ማስታወቂያ!

በ2014 ዓ.ም ወደ ኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ የተመደባችሁ አዲስ ገቢ የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎች ሚያዝያ 28 እና 29/2014 ዓ.ም ሪፖርት እንድታደርጉ እያሳሰብን ወደ ዩኒቨርሲቲው በምትመጡበት ጊዜ
  •  የ1ዐኛ እና 12 ክፍል ብሔራዊ ፈተና ሰርተፊኬት
  • ከ9-12 ክፍል የተማራችሁበትን ትራንስክሪፕት
  •  4 ፓስፖርት ሳይዝ ፎቶግራፍ
  •  አንሶላና ብርድልብስ
  • የስፖርት ልብስና ጫማ
ይዛችሁ እንድትመጡ እያስታወቅን ከላይ ከተጠቀሱት ቀናት ቀድሞም ሆነ ዘግይቶ የሚመጡ ተማሪዎችን የማናስተናግድ መሆኑን እናስታውቃለን።
ሬጅስትራርና አልሙናይ ማናጅመንት ዳሬክቶሬት

የ2014 ዓ.ም የ2ኛ ድግሪ ትምህርትን በተመለከተ

በ2014 ዓ.ም ዩኒቨርስቲያችን ከሜትሮፖሊታን ወደ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ መቀየሩን ተከትሎ የ2014 ዓ.ም ምዝገባ መተላለፉ ይታወቃል። በመሆኑም አዳዲስ የ2ኛ ድግሪ ፕሮግራሞች በ”Masters of Education” በቅርቡ ምዝገባ ለመጀመር ዝግጅት እየተጠናቀቀ መሆኑን እየገለጽን፣ ቀደም ብሎ ምዝገባ የተካሄደባቸው የ2ኛ ድግሪ ፕሮግራሞች ምዝገባው በ”Online” እስከ ሚያዝያ 18/2014 ዓ.ም መቀጠሉን እናሳውቃለን።
ማሳሳቢያ: ከዚህ በፊት በ”Online” ለተመዘገባችሁ ለምዝገባ የከፈላችሁት ብር ታሳቢ የምናደርግ መሆኑን እንገልጻለን፡፡
– ለፕሮግራሞቹን ዝርዝርና የማመልከቻ ሊንክ/የሚቀጥለውን ማስፈንጠርያ ይጫኑ::
– ለበለጠ መረጃ: +251118723289 ወይም
– የየኮሌጅ ሬጂስትራር በአካል በመገኘት ይጠይቁ።
                                                                                               የድህረ ምረቃ ት/ቤት

ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ፋካልቲ የሚያዘጋጀው የእውቀት ማጋራት መርሐ ግብር መጠናከርና በሌሎች መለመድ እንዳለበት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ገለፁ።

የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ፋካልቲ ሦስተኛውን የእውቀት ማጋራት መርሐ-ግብር በ11/08/2014ዓ.ም ባካሄደበት ወቅት የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ብርሃነመስቀል ጠና፣ ፋካልቲው የሚያዘጋጀው ወርሃዊ የእውቀት ማጋራት መርሐ-ግብር እንደጥሩ ልምድ ተወስዶ ከዚህ የበለጠ በሀገር ዓቀፍ ደረጃ ማደግ እና መስፋት እንዳለበት ገልፀዋል። ተማሪዎችም እውቀት የሚቀስሙበት በመሆኑ ልምዱ በሁሉም ፋካልቲዎች መለመድ አለበት ብለዋል።
የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ሽመልሽ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር፣ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ፋካልቲ ፈር ቀዳጅ ሆኖ ብዙ ጥናታዊ ጽሑፎችን እና መድረኮችን በተከታታይ በማዘጋጀት በግንባር ቀደምትነት የሚተጋ ፋካልቲ በመሆኑ ለማመስገን እወዳለሁ ካሉ በኋላ፣ የዛሬው ውይይት ዓለም ዓቀፋዊ እና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የተዘጋጀ እንደመሆኑ መጠን ውይይቱን አስፈላጊና የተለየ እውቀት የሚገኝበት ነው ሲሉ ተናግረዋል። ይህ ዓይነቱን እውቀት የማጋራት መድረክ የተወሰኑት ፋካልቲዎች የጀመሩ ቢሆንም የተቀሩት ፋካልቲዎች ከዚህ አይነቱ መድረክ ተምረው ብዙ መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
የቢ.ኢ.ፋ ዲን የሆኑት ዶ/ር ኃይለሚካኤል ሙሌ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ባሰሙበት ወቅት፣ በፋካልቲያችን ደረጃ አቅደን ከምንሰራቸው ሥራዎች ውስጥ አንዱ ይህ የእውቀት ማጋራት ሲሆን፣ በቀጣይ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎትን የተመለከቱ ሁለት መድረኮች በተከታታይ እንደሚቀርቡና የኒውስሌተር ዝግጅትም እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል። ከዚህም በተጨማሪ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ጉዳይ በአብዛኛው የጋራ ጉዳይ በመሆኑ፣ ሰፋ ባለ መድረክ የሚያወያዩ ሀገራዊ እና ዓለምዓቀፋዊ አጀንዳዎችን በመቅረፅ እንደሚቀርቡ አሳውቀዋል።
በመርሐ-ግብሩ ላይ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ እንዲሁም የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት በዓለም ኢኮኖሚ ላይ ያስከተሉትን ተፅዕኖ እና ተያያዥ ጉዳዮችን የተመለከቱ ሁለት የውይይት መነሻ ጽሑፎች የፋካልቲው መምህራን በሆኑት በአቶ ዮናስ አብርሃ እና በአቶ አብደላ ቆሳ ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
                                                           የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት

KUE Confers with Scholars and High-level Leaders upon Its Transitional Roadmap

April 16, 2022
Kotebe University of Education had a high-level consultative meeting with a panel of scholars, and high-level ministerial and managerial leaders on its transitional roadmap. The participants of the panel discussion consisted of a state minister, renowned education professors and KUE’s Board, management and technical team, and steering committees coordinators.
At the outset of the meeting, Honourable Dr. Berhanemeskel Tena, the President of the University, and Dr. Samuel Kefle, the State Minister, delivered the welcome speech, and opening remarks respectively. Dr. Fekede Tuli, the technical team leader, also gave a brief introduction to the transitional roadmap. Following that, four scholars, namely Prof. Yalew Endawoke, Prof. Belay Tefera, Dr. Wondweson Tamirat, and Dr. Meskerem Lechisa reviewed the roadmap document and presented their unreserved enlightenment on it at the event. The technical team coordinators also had the opportunity to reflect on the points made by the reviewers of the transitional roadmap document.
In addition to the professors who presented their views at the forum today, the President said other high-level academic experts also took the document and reviewed it, and once the document has been properly developed, it will be presented to stakeholders at a broader stage.
Eventually, Ato Abadula Gemeda, the KUE’s Executive Board Chairperson, remarked that Kotebe has to fully exploit the expertise of the scholars to bring change in the quality of education that is desired to happen in the nation.
It is well recalled that Kotebe rebrands itself from a metropolitan-oriented institution to an education university.
                                                          Communication Affairs Directorate

የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ መላው አመራሮች በዩኒቨርሲቲው ፍኖተ-ካርታ እና አጠቃላይ የመምህራን ማህበር ማቋቋሚያ ላይ መከሩ

(ማክሰኞ 27/07/2014)

የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ አመራሮች በዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት በተከበሩ ዶክተር ብርሃነመስቀል ጠና ሰብሳቢነት በዩኒቨርሲቲው ፍኖተ-ካርታ ላይ በሠፊው መክረው በሂደቱም ላይ የነበረው ምቹ ሁኔታ እና ተግዳሮቶች ውይይት ተደርጎባቸው መግባባት የተደረሰባቸው ሲሆን፣ ሰነዱ በተሠጠው ግብዓት ዳብሮ ለውሳኔ ለትምህርት ሚኒስቴር እንዲቀርብ ሆኗል።
በሌላ በኩል ዩኒቨርሲቲው የመምህራን ማህበር ለማቋቋም የማህበሩ መተዳደሪያ ደንብ የመነሻ ሀሳቡ በጊ/የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሽመልስ ዘውዴ ቀርቦ የመምረጫ ጊዜ ሠሌዳ ተቀምጦ ስብሰባው ተጠናቋል።
                                       የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት

ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ በከፍተኛ ትምህርት የመውጫ ፈተና የአፈፃፀም መመሪያ ላይ ተወያየ።

የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ኃላፊዎች፣ መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች የትምህርት ሚኒስቴር ባወጣው የከፍተኛ ትምህርት የመውጫ ፈተና አፈፃፀም መመሪያ ዙሪያ ላይ መጋቢት 29 ቀን 2014 ዓ.ም ውይይት አካሄዱ።

የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶክተር ሽመልስ ዘውዴ ለውይይቱ የመነሻ ሃሳብ ባቀረቡበት ወቅት፣ ለመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎች የተዘጋጀው የከፍተኛ ትምህርት የመውጫ ፈተና የትምህርት ጥራትን ከማረጋገጥ ጎን ለጎን በዩኒቨርሲቲዎች መካከልም የተወዳዳሪነትን መንፈስ ያጎለብታል ብለዋል፡፡ ዶክተር ሽመልስ በመቀጠልም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሩቃን ገበያው የሚፈልገውን አቅምና ብቃት ያሟሉ መሆናቸውን በፈተና መፈተሽ አስፈላጊ በመሆኑ፣ ይህ የከፍተኛ ትምህርት የመውጫ ፈተና አሰጣጥ መመሪያ መዘጋጀቱን አስረድተዋል፡፡

የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት የተከበሩ ዶክተር ብርሃነመስቀል ጠና በዚሁ ጊዜ በሰጡት አስተያየት የከፍተኛ ትምህርት የመውጫ ፈተና አሰጣጥ መመሪያው ተማሪዎች ብቻ ሳይሆኑ መምህራንና ተቋማትም ተወዳዳሪ እና ብቁ ሆነው የሚገኙበትን አሰራር ስለሚፈጥር፣ ለአተገባበሩ ልዩ ትኩረት መስጠትና በዩኒቨርሲቲያችን ደረጃም አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ማድረግ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡

በመመሪያው ላይ በተደረገው ውይይት ተሳታፊ የነበሩት መምህራንም የትምህርት ጥራትን ለማምጣት የከፍተኛ ትምህርት የመውጫ ፈተና አሰጣጥ መመሪያውን ከመተግበር ባሻገር ሥርዓተ ትምህርቱን ማሻሻል፣ የዩኒቨርሲቲዎችን የቅበላና የትምህርት አሰጣጥ መርሐ-ግብርን ማስተካከል፣ ለትምህርት ጥራት የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ማሟላት፣ ጊዜው አጭር እና ውሳኔውም የፈጠነ በመሆኑ፣ መመሪያውን የሚያስፈፅም ራሱን የቻለ ጽሕፈት ቤት በዩኒቨርሲቲያችን ደረጃ ማቋቋም አስፈላጊ ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት