(ኮትዩ፣ ታህሳስ 15 ቀን 2018 ዓ.ም) – ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ በቅርቡ እያካሄደ ባለው የተቋማዌ ለውጥ አሠራር መሠረት ለተሾሙ አዳዲስ አመራሮች በኢ-ለርኒንግ ዙሪያ የተሰጠውን ገለጻ በንግግር የከፈቱት የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዘዳንት ዶ/ር አለባቸው ከሚሶ፣ የውይይት መድረኩ ያለንን ልምድና ዩኒቨርሲቲው ለማሳካት ያቀዳቸውን ተግባራት ለማሳለጥ የሚያግዝ በመሆኑ ያለውን ጠቀሜታ በመግለጽ ትኩረት እንደሚያስፈልገው ገልጸዋል፡፡
በእስካሁኑ ሂደት በዩኒቨርሲቲው ሲሰጥ በነበረው የኢ-ለርኒንግ ትምህርት ዙሪያ የተገኙ ውጤቶችንና ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በማስመልከት ገለጻ ያደረጉት የኢ-ለርኒንግ ማኔጅመት ዳይሬክተር ዶ/ር ደረሰ ተርፋ፣ የኢ-ለርኒንግ እና ኢ-ሼ (e-Learning and e-SHE) አሰራሮችን ከማስተዋወቅ በተጨማሪ ዲጂታል ቴክኖሎጂን በአግባቡ ለመጠቀም በትብብር መስራት እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፣ ለቀጥታ የኢ-ለርኒንግ መርሐግብር የሚያስፈልጉ የካሜራ እና የስቱዲዮ መሳሪያዎችን ማሟላትና ክፍሉን እንደገና ማዋቀር እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡
በኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የኢ-ሼ (e-SHE) የሥርዓተ ጾታ ተወካይ ወ/ት ሃና ኩመራ በበኩላቸው ሀገራዊ የዲጂታል ትምህርትን በማስመልከት እንደገለጹት፣ የተቋሙ ዋና ዓላማ የኢትዮጵያን የመማር ማስተማር ሂደት በዲጂታል ቴክኖሎጂ ማገዝ በመሆኑ፣ ከተለመደው የሰሌዳ እና በክፍል ውስጥ ከተገደበው የመማር ማስተማር ሂደት በመውጣት በዲጂታል ማስተማርና መማር፣ የትምህርት ይዘቶችን በሀገር ውስጥ ምሁራን በመቅረፅ ለተማሪዎች መስጠት እንዲቻል በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡





