Skip to content

“በአንድ ጀንበር 700 ሚሊዮን ችግኝ መትከል” መርሐግብር በኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ መምህራን እና የአስተዳደር ሠራተኞች በሰፊው ተከናወነ።

በወንድይራድ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግቢ ውስጥ በተካሄደው የችግኝ ተከላ መርሐግብር ላይ የተገኙት የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ዶ/ር ብርሃነመስቀል ጠና፣ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ “በመትከል ማንሰራራት!” በሚል መሪ ቃል በቅርቡ በዩኒቨርሲቲው ግቢ እና በወንድይራድ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ችግኝ መትከሉን አስታውሰው፣ በዛሬው ዕለትም የተከናወነው የችግኝ ተከላ ደግሞ “በአንድ ጀንበር 700 ሚሊዮን ችግኝ መትከል” በሚል መሪ ቃል በክቡር የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረውን የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የሚያስቀጥል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በመላው ሀገሪቱ እየተካሄደ ያለውን ይህን የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ መርሐግብር ተግባራዊ ለማድረግ ዛሬ የተከልናቸውን ችግኞች በመንከባከብ የተሻለች አረንጓዴ ፣ የተፈጥሮ ምህዳሯ የተስተካከለ ሀገር ለትውልድ ለማቆየት ዛሬ እንተክላለን፤ በቀጣይም የተከልነውን በቅርበት የመንከባከብ ኃላፊነት አለብን ብለዋል ፕሬዚዳንቱ።
በዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ በተካሄደው የችግኝ ተከላ ከ3,000 በላይ ልዩ ልዩ ችግኞች የተተከሉ ሲሆን፣ በመርሐግብሩ ላይም በየካ ክፍለ ከተማ የወረዳ 11 ጽ/ቤት ሥራ አስፈጻሚ እና አመራሮች፣ እንዲሁም የወንድይራድ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አብረውን ተክለዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *