በዩኒቨርሲቲው የግማሽ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ውይይት ተካሄደ፡፡

በኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የግማሽ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ላይ በተደረገው ውይይት፣ የዩኒቨርሲቲው መምህራን እና የአስተዳደር ሠራተኞች ተሳትፈዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ብርሃነመስቀል ጠና በመክፈቻ ንግግራቸው የግማሽ ዓመት የሥራ አፈጻጸሙ በተቀናጀ ቡድናዊ ሥራ (team work ) የተመዘገበ የጋራ ውጤት ነው ፤ በመሆኑም ለቀጣይ የተሻለ ሥራ የዚህኛውን ሴኬት፣ ተግዳሮት እና እንዲሁም ለተሻለ አፈፃፀም በተወሰዱት አማራጭ መፍትሔዎችን በደንብ መገምገም ቀጣይ ቀሪ ሥራዎችን በተሻለ ለመከወን ይረዳል ብለዋል።
የዩኒቨርሲቲው የስትራቴጂክ ዕቅድ ጽ/ቤት ሥራ አስፈጻሚ አቶ አስናቀ ጉዲሳ፣ የዩኒቨርሲቲው ቁልፍ አፈጻጸም አመልካቾች ሰነድ ከትምህርት ሚኒስቴር እና ከዩኒቨርሲቲው የበላይ አመራሮች ጀምሮ ባለው መዋቅር ሁሉ በየደረጃው የተፈራረሙት እና ተግባራዊ ማድረግ የጀመሩት መሆኑን በመጥቀስ፣ በግማሽ ዓመቱ በታየው የሥራ አፈጻጸም የዩኒቨርሲቲው የትኩረት አቅጣጫ ልየታ፣ በመማር ማስተማር፣ በጥናትና ምርምር፣ በማህበረሰብ አገልግሎት እንዲሁም በአስተዳደር ዘርፍ ውጤታማ ስራዎች መሰራታቸውን አመልክተዋል፡፡
የውይይቱ ተሳታፊዎችም የሆኑት (የዩኒቨርሲቲው መምህራን እና የአስተዳደር ሠራተኞች) በሪፖርቱ የተሰማቸውን ደስታ በመግለጽ፣ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ በመሠረት ልማት ግንባታም ሆነ በሌሎች ዘርፎች እየታዩ ያሉ ለውጦች እና ስኬቶች አስደሳችና የተሻለ ምቹ የትምህርት ተቋም ለመፍጠር ማናጅመንቱ እያደረገ ያለውን ጥረት ተቋሙ ገና አሁን የዩኒቨርሲቲ ገጽታ እየተላበሰ ያለ በመሆኑ አመስግነው ሥራው ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል። አያይዘውም የሀገሪቱን የትምህርት እና የመምህርነት ሙያ ችግር ለመፍታትም በጥናት ላይ የተመሠረተ ምክረ ሃሳብ ለማቅረብ የሚያስችል ሥራ መሥራት ለነገ የማይባል እንደሆነ በማንሳት አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
በመጨረሻም ፕሬዚዳንቱ መድረኩን ሲያጠቃልሉ ቀደም ሲል በበጀት ዓመቱ ለማሳካት የታቀደውን ሙሉ ለሙሉ ያሳካ መሆኑን በመግለጽ፣ ነገር ግን በተገኘው ውጤት መዘናጋት ሳይሆን በቀሪዎቹ ጊዜያትም የዓመቱን ጠቅላላ ዕቅድ በተሳካ ሁኔታ ለመፈፀም በርብርብ እና በኃላፊነት ስሜት መስራት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡
 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *