Skip to content

ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲን ለዘንድሮ አዲስ ገቢ ተማሪዎቹ ገለጻ አደረገ

(ኮትዩ፣ ጥቅምት 20 ቀን 2018 ዓ.ም) ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲን በዘንድሮው ዓመት ለተቀላቀሉ የመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎች ስለዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማር ሂደት እና የአገልግሎት አሰጣጥን አስመልክቶ የተካሄደውን የገለጻ መርሐግብር የከፈቱት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዘዳንት ዶ/ር ተሾመ ነቃጥበብ “እንኳን ደህና መጣችሁ” ካሉ በኋላ፣ የዩኒቨርሲቲ ትምህርት ከመደበኛው ትምህርት በተለየ ሁኔታ ተማሪዎች ራሳቸውን ፈልገው የሚያገኙበት እና በራስ የመተማመን መንፈስ የሚያዳብሩበት የእውቀት ምዕራፍ በመሆኑ በትምህርታቸው ስኬታማ እንዲሆኑ ጠንክረው መስራት እንዳለባቸው ገልፀዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲ የራሱ ህግና ሥርዓት ያለው በመሆኑ ይህን ህግ በማክበር ተማሪዎቹ በቆይታቸው ስኬታማ እንዲሆኑም ለመጡበት የትምህርት ዓላማ ቅድሚያ መስጠት እንደሚጠበቅባቸው ፕሬዘዳንቱ አሳስበዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዘዳንት ዶ/ር ፈቀደ ቱሊ በበኩላቸው፣ እንኳን ወደ ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ በደህና መጣችሁ በማለት፣ ቆይታችሁ የተሳካና አስፈላጊውን ዕውቀት የምትጨብጡበት እንዲሆን አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አጠናቆ ተቀብሏችኋል ብለዋል፡፡
የተማሪዎች አገልግሎት ዲን፣ የተማሪዎች ሰብዕና ግንባታ ምክትል ዲን፣ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች አካቶ ትግበራ ሥራ አስፈጻሚ፣ የሬጅስትራር እና አልሙናይ ዳይሬክተር፣ የኢ-ለርኒንግ ዳይሬክተር፣ የቤተ-መጻሕፍት አገልግሎት ሥራ አስፈጻሚ፣ የቅድመ ምረቃ ፕሮግራሞች አስተባባሪ፣ የሰላምና ደህንነት አገልግሎት ምክትል ሥራ አስፈጻሚ እና የአካዳሚክ ፕሮግራሞች ዳይሬክተር ተማሪዎቹ በሚኖራቸው ቆይታ ስለሚያገኙት አገልግሎት፣ ስለትምህርት አሰጣጥና ስለ ውጤት አያያዝ፣ ማክበር ስለሚገባቸው መመሪያዎች፣ ራሳቸውን ከኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ጠብቀው ስኬታማ እና ብቁ ዜጋ በመሆን ለምረቃ ስለሚበቁባቸው ስልቶች ለተማሪዎቹ ገለጻ አድርገዋል፡፡
በገለጻ መርሐግብሩ ላይ የሥነ-ጥበባት ትምህርት ክፍል መምህራንና ተማሪዎች ልዩ ልዩ ጣዕመ ዜማዎችን አሰምተዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *