Skip to content

ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ለተማሪዎቹ በሰብዕና ግንባታ ላይ ያተኮረ ስልጠና ሰጠ

(ኮትዩ፣ ጥቅምት 27 ቀን 2018 ዓ.ም)- በሰብዕና ግንባታ ላይ ያተኮረው ስልጠና የከፈቱት በዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዘዳንት ልዩ ረዳት ዶ/ር መስፍን ደጀኔ፣ የሰብዕና ግንባታ ስልጠና ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ በሚኖራቸው ቆይታ እንዴት ውጤታማ እንደሚሆኑና የሚገጥሟቸውን ችግሮች እንዴት መፍታት እንደሚችሉ የሚያግዝ በመሆኑ ስልጠናው የሚኖረውን ጠቀሜታ ገልጸው፤ ተማሪዎቹ ስልጠናውን በንቃት እንዲከታተሉ አሳስበዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው የኢሞሽናል ኢንተለጀንስ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር አልማው ክፍሌ፣ የስልጠናው ዋና ዓላማ ተማሪዎች በትምህርታቸው ስኬታማ የሚያደርጋቸውን ሰብዕና እንዲገነቡና የሚገጥሟቸውን ዘርፈ ብዙ ተግዳሮቶች ተጋፍጠው በአዎንታዊ መልኩ መፍታት የሚያስችል ጠንካራ ማንነት እንዲኖራቸው መርዳት እና የህይወት ክህሎት እንዲያዳብሩ ማድረግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም፣ መልካም ሰብዕና እንዲኖራቸው፣ ጠንካራ የስነልቦና ዝግጅት እንዲያድርጉ፣ የፈተና ጭንቀትን እንዲያስወግዱና የጭንቀት መከላከያ ዘዴዎችን እንዲያውቁ፣ ለትምህርታቸው ትኩረት እንዲሰጡ፣ በራስ መተማመንን እንዲያብሩ እና በወደፊት ህይወታቸውም ስኬታማ እንዲሆኑ መርዳት ከዚህ ስልጠና እንደሚጠበቅ አክለው ገልጸዋል፡፡
ለሁለት ቀናት በሚቆየው በዚህ ስልጠና የአንደኛ፣ የሁለተኛ፣ የሦስተኛ እና የአራተኛ ዓመት መደበኛ የዲግሪ መርሐግብር ተማሪዎች ተሳታፊ መሆናቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *