(ኮትዩ፣ መስከረም 30/2018 ዓ.ም) የኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስቴር በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ በ2018 ዓ.ም ሊተገበሩ የታቀዱ ቁልፍ የውጤት አመላካቾች (KPIs) ከመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የአፈጻጸም ውል ስምምነት ተፈራርሟል፡፡
በካፒታል ሆቴል በተደረገው የፊርማ ሥነስርዓት ላይ የተገኙት የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ ዩኒቨርሲቲዎች ለተፈራረሙት ውል ተግባራዊነት በቁርጠኝነት መስራትና የልህቀት ማዕከል ለመሆን በየአካባቢያቸው በሚገኙ የተፈጥሮ ሀብቶች ላይ የትኩረት መስካቸውን ለይተው መስራት እንዳለባቸው አሳስበው፤ ስምምነቱ በዋናነት መረጃን መሰረት ያደረገ እና ተቆጥሮ የሚመዘን በመሆኑ፣ ዩኒቨርሲቲዎች የወሰዱትን ተግባራት አፈጻጸም ጥራትና ተአማኒነት ባለው መረጃ አስደግፈው ማቅረብ እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።