(ኮትዩ፣ ጥቅምት 13 ቀን 2018 ዓ.ም)- ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ እና የአዲስ አበባ ሴቶች፣ ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳዮች ቢሮ በጥናትና ምርምር፣ በትምህርትና በአቅም ግንባታ ስልጠናዎች ላይ በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ዛሬ በቢሮው በተዘጋጀ የፊርማ ሥነስርዓት፣ የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ዶ/ር ተሾመ ነቃጥበብ እና የአዲስ አበባ ከተማ ሴቶች፣ ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ቆንጂት ደበላ ተፈራርመዋል።
አቶ መኩሪያ መኳንንት የቢሮው የጥናት ፕሮጀክቶች ዳይሬክተር ተወካይ በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ዝግጅቱን ያስጀመሩ ሲሆን፣ የዛሬው ስምምነት ሁለቱ ተቋማት እስከ ዛሬ በጋራ ሲያከናውኗቸው የቆዩትን ሥራዎችን በሰነድ አጠናክሮ የማስቀጠል ዓላማ ያለው መሆኑን ገልጸው፣ ቀደም ሲል ሁለቱ ተቋማት በጋራ የሠሯቸውን ፕሮጀክቶች አስተዋውቀዋል።
የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ዶ/ር ተሾመ ነቃጥበብ፣ ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ እንደየትምህርት ተቋምነቱ በመሆኑ፣ ሀገራቸውን የሚጠቅሙ፣ ኃላፊነት የሚሰማቸው እና በስነምግባር የታነፁ ዜጎች የሚፈጠሩበት በመሆኑ እነዚህ ዛሬ የሚቀርቡት ጥናቶች የተሻለ ዜጋ ለማፍራት መፍትሄ የሚፈለግባቸው መሆናቸውን በመጠቆም ዛሬ የተደረገው የጋራ ስምምነትም ይህን መሰል ጠቃሚና ተሻጋሪ ተግባራትን በቀጣይም ለማከናወን ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።




