በኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ እና በአፋር ትምህርት ቢሮ . መካከል ዛሬ ጥር 16 ቀን 2017 ዓ.ም የተፈረመው ስምምነት፣ በአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የሚገኙ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን በማብቃት ሞዴል የትምህርት ተቋም ለማድረግ የሚያስችሉ የሥልጠና እና የምርምር ሥራዎችን በጋራ ለመስራት የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል፡፡
የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ዶ/ር ብርሃነመስቀል ጠና በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፣ በሀገራችን የትምህርት መስክ ዘመናትን የተሻገረ የማይተካ ውጤታማ አገልግሎት ያለው ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ፣ በተለይም የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ሆኖ ለተለየ ተልዕኮ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ የሀገሪቱን የትምህርት ጥራት ለማሻሻል በከፍተኛ ትኩረት እየሠራ መሆኑንና፣ በዚህ ረገድ ከሚተገብራቸው ሥራዎች አንዱ አጠቃላይ ትምህርቱን ማገዝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም በትምህርቱ መስክ ሁለንተናዊ ለውጥ ለማምጣት ብሎም ሞዴል የ2ኛ ደረጃ ት/ቤቶችን ለመፍጠር በሚቻልበት ክልሉን የመደገፍ ኃላፊነት መውሰዳቸውን በፊርማው ሥነሥርዓት ላይ ገልጸዋል፡፡
የአፋር ብሔራዊ ክልልላዊ መንግሥት ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱሀሰን ያዮ በበኩላቸው፣ ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ በትምህርት ጉዳይ አንጋፋ እንደመሆኑ መጠን ከዩኒቨርሲቲው ጋር በትብብር ለመስራት እና አስፈላጊውን ትብብር ለማድረግም ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸው፣ ከዚህ ከፍተኛ ልምድ፣ የሰው ኃይል እና የተፈተኑ ዕውቀቶችን ካካበተ ተቋም ጋር አብሮ ለመሥራት በመቻላቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል፡፡