Skip to content

ዓለምቀፍ የፀረ ሙስና ቀንን ምክንያት በማድረግ በዩኒቨርሲቲው ውይይት ተካሄደ

(ኮትዩ፣ ህዳር 29 ቀን 2018 ዓ.ም) – “ትውልድን በሥነምግባር፣ ተቋምን በአሰራር!” በሚል መሪ ቃል 22ኛውን ዓለምአቀፍ የፀረ ሙስና ቀን ምክንያት በማድረግ በኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የተዘጋጀውን የውይይት መርሐግብር በንግግር የከፈቱት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዘዳንት ዶ/ር ተሾመ ነቃጥበብ፣ እንደ ዩኒቨርሲቲ ጥሩ ዜጋ የመቅረጽ ኃላፊነት የተጣለብን በመሆኑ፣ ስነምግባር ያለው ትውልድ ለማፍራትም በቅድሚያ ራሳችን አርአያ ሆነን መገኘት ይኖርብናል ብለዋል፡፡
የሥራ ኃላፊዎች ጥሩ ሞዴል በመሆን አሰራራቸውንና ተቋማቸውን ማደስ አለባቸው ያሉት ፕሬዘዳንቱ፣ ታማኝና እውነተኛ ማህበረሰብን በመፍጠር ረገድ አዎንታዊ ለውጥ ለማምጣትም ምሁራን በህዝቡ አእምሮ ላይ መስራት ይጠበቅባቸዋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በመርሐ ግብሩ ላይ በፌዴራል ጸረ ሙስና ኮሚሽን የተዘጋጀ ሰፊና ጥልቅ የፀረ ሙስና ንቅናቄ ሰነድ በድምፅ የቀረበ ሲሆን፣ የፀረ ሙስናን ቀን በዓመት አንድ ጊዜ ከማክበር በዘለለ በዩኒቨርሲቲው ለሙስና የሚዳርጉ አሰራሮችን በዲጂታል ቴክኖሎጂ በመታገዝ ከማስቀረት በተጨማሪ በቤተሰብ፣ በህብረተሰብ፣ በተቋም እና በሀገር ደረጃ መስናን የሚፀየፍና የሚታገል ትውልድ ለመፍጠር የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ የበኩሉን ድርሻ መወጣት አለበት ተብሏል፡፡
የዩኒቨርሲቲው የሥነምግባር መከታተያ ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር አዲስዓለም በቀለ የዕለቱ መርሐግብር የተሳካና የፀረ ሙስና ንቅናቄውም ቀጣይነት ያለው መሆኑን ጠቅሰው፣ በመርሐግብሩ ላይ ለተሳተፉ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች እና ማህበረሰብ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በመጨረሻም የዩኒቨርሲቲው ፕሬዘዳንት እና ምክትል ፕሬዘዳንቶች ከሥነምግባር መከታተያ ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት ጋር የሀብት ምዝገባ ሰነድ ርክክብ አደርገዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *