Skip to content

“ዝቅተኛ የማሳለፍ ምጣኔ ያላቸው ትምህርት ቤቶችን ማጠናከር ያስፈልጋል!” – ዶ/ር ተሾመ ነቃጥበብ

(ኮትዩ፣ ጥቀምት 18 ቀን 2018 ዓ.ም)- የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ከየካ፣ ለሚ ኩራ፣ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተሞች ለተውጣጡ ርዕሳነ መምህራን፣ የክፍለ ከተማዎቹ የትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊዎች በዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ለመወያየት ያዘጋጀውን መድረክ በንግግር የከፈቱት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዘዳንት ዶ/ር ተሾመ ነቃጥበብ፣ ዩኒቨርሲቲው እስካሁን ከሚሰጠው የማህበረሰብ አገልግሎት በተጨማሪ ዝቅተኛ የማሳለፍ ምጣኔ ያላቸው ትምህርት ቤቶች ላይ ትኩረት በማድረግ ማጠናከር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ባለፈው ዓመት በአዲስ አበባ የሚገኙ 5 ትምህርት ቤቶችን በሞዴልነት ይዞ ልዩ ድጋፍ ሲያደርግ የቆየ ሲሆን፣ ቀዘንድሮው ዓመት ደግሞ ወደ 8 ትምህርት ቤቶች በማሳደግ የማህበረሰብ አገልግሎት ለመስጠት ከሚያከናውናቸው ተግባራት በተጨማሪ ብዙ ተማሪዎችን የማያሳልፉ ትምህርት ቤቶችን በመለየት የተለየ ትኩረት በመስጠት ውጤታማ ሥራ መስራት እንደሚያስፈልግም ፕሬዘዳንቱ ዶ/ር ተሾመ አስገንዝበዋል፡፡
በዚሁ ወቅት በተካሄደው ውይይትም ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ከትምህርት ቤቶቹ ጋር መስራት ከጀመረ ወዲህ በተግባር የሚታይ የውጤት መሻሻል መመዝገቡን በመጥቀስ፣ በቀጣይም በመምህራን የአቅም ግንባታ ስልጠና፣ በተማሪዎች ስነምግባር፣ የአይ.ሲ.ቲ. እና የላቦራቶሪ ግብዓትን በማሟላት ረገድ እንዲሁም የቆዩ ኬሚካሎችን በማስወገድ ረገድ ዩኒቨርሲቲው አስፈላጊውን እገዛ እንዲያደርግላቸው ከየትምህርት ቤቱ የመጡ ርዕሳነ መምህራን ጠይቀዋል፡፡
የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ጽ/ቤት ኃላፊ ዶ/ር ተሾመ ቶልቻ ዩኒቨርሲቲው ለትምህርት ቤቶች የሚያደርገው ድጋፍ ውጤት እያመጣ በመሆኑ ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸው፣ ይህ ፕሮጀክት የአንድ ወገን ብቻ ሳይሆን የሁሉም ባለድርሻ አካላት በመሆኑ ጥምረትን መፍጠር፣ ሁሉንም ትምህርት ቤቶች በአንድ ጊዜ ማገዝና ማዳረስ ስለማይቻል በተለይም እንደ ላቦራቶሪ አይነት አገልግሎቶችን በማዕከል ደረጃ መስጠት አስፈላጊ ስለሆነ የሳይንስ ሼርድ ላቦራቶሪን እንደ ሞዴል መጠቀምና አስፈላጊ ግብዓቶችን በሂደት ለሌሎች ትምህርት ቤቶችም ማዳረስ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡
የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክተር ዶ/ር መርዕድ ቱፋ የማህበረሰብ አገልግሎት ዋና ዓላማ ትምህርት ቤቶችን በስልጠናና በግብዓት በመደገፍ የትምህርት ጥራትን ማምጣት በመሆኑ በእስካሁኑ ሂደት የተሰሩ ስኬታማ ስራዎችን መገምገም፣ መምህራንን በአቅም ግንባታ ስልጠና ማገዝ፣ በተማሪዎች ስነምግባር ላይ መስራት፣ ለዚህም የወላጆችን ተሳትፎ ማጠናከር፣ የልምድ ልውውጥ ማዕከል መፍጠር በቀጣይም ትኩረት የሚሰጣቸው ጉዳዮች መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
በውይይቱ ላይ ከሦስቱም ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ 20 ርዕሳነ መምህራን፣ የየክፍለ ከተማዎቹ የትምህርት ጽ/ቤቶች ኃላፊዎች፣ የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ኮሌጆች ዲኖች እና የትምህርት ክፍሎች ኃላፊዎች የተሳተፉ ሲሆን፣ በዩኒቨርሲቲው በኩል ለየትምህርት ቤቶቹ የሚሰጠውን የማህበረሰብ አገልግሎት በጋራ ጥረት ለማሳካት ሁሉንም ትምህርት ቤቶች ተደራሽ ለማድረግ የትራንስፖርት አገልግሎትን ከማመቻቸት ጀምሮ ከቀድሞው በተሻለ ሁኔታ ትስስር በመፍጠር አጠናክሮ ለመቀጠል ከመግባባት ላይ ተደርሷል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *