Skip to content

የሴት ተመራማሪዎች የምርምር ልምድ ልውውጥ ተካሄደ

(ኮትዩ፣ የካቲት 6 ቀን 2018 ዓ.ም) – የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የሴት ተመራማሪዎች ማኅበር ያዘጋጀው የምርምር ልምድ ልውውጥ በዩኒቨርሲቲው የስብሰባ አዳራሽ ተካሄዷል፡፡
የልምድ ልውውጡን መድረክ በንግግር የከፈቱት የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ዶ/ር ተሾመ ነቃጥበብ፣ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ምርምር ማካሄድ ከተቋማዊ ተልዕኮዎች መካከል አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፣ የሴቶች በምርምር ተግባር ላይ መሳተፍ ግን የእኩልነት ጥያቄ ብቻ ሳይሆን የብቃት መለኪያ በመሆኑ፣ ሴት ተመራማሪዎች ከአውሮፓ ንድፈሃሳብ ባሻገር በማህበረሰባችን ውስጥ ያለውን እውነተኛ የጾታ እና ማኅበረሰብ መስተጋብር በማጥናት የምርምራቸውን ግኝት ይፋ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡
በጾታ እና ማኅበረሰብ መካከል ያለው መስተጋብር ከአንድ ማኅበረሰብ በዘለለ ሀገራዊ ጠቀሜታ ያለው ጉዳይ ስለሆነም፣ በዚህ ረገድ የሚካሄደው የምርምር ልምድ ልውውጥ ለአቅም ግንባታ የራሱን ድርሻ ያለው ከመሆኑም በተጨማሪ የሴቶች በጥናትና ምርምር ላይ መሳተፍ በዩኒቨርሲቲ የሚካሄደውን ምርምር የጥራት ደረጃ እንደሚጨምር እና ለዚህም ስኬት ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ለሴት ተመራማሪዎችና የምርምር ሥራዎቻቸው ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥ ገልጸዋል፡፡
የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የምርምርና የማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዘዳንት ዶ/ር ቴዎድሮስ ሙሉጌታ፣ የኢትዮጵያ የሴት ተመራማሪዎች ማኅበር መቋቋም ለሴቶች የተሻለ ዕድል እንደሚፈጥር ገልጸው፣ ዩኒቨርሲቲያችንም ቀደም ሲል ሴቶችን በምርምር ለማበረታታት የጀመረውን እንቅስቃሴ አጠናክሮ እንዲቀጥል ይህ ዓይነቱ መድረክ አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የሴት ተመራማሪዎች ማኅበር ፕሬዘዳንት ዶ/ር አልማዝ ደብሩ፣ የልምድ ልውውጥ መድረኩ ተሳታፊዎቹን እንኳን ደህና መጣችሁ ካሉ በኋላ፣ የኢትዮጵያ የሴት ተመራማሪዎች ማኅበር ሕጋዊ ዕውቅና አግኝቶ መመሥረቱን፣ ይህንኑ ሂደት ተከትሎ የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የሴት ተመራማሪዎች ማኅበርም የራሱን የሥራ አስፈፃሚዎች በመምረጥ እንቅስቃሴ መጀመሩን ጠቁመው፣ ዋና ዓላማውም ሴት ተመራማሪዎችን በትምህርት እርከን ወደፊት ማምጣት ብቻ ሳይሆን በምርምርና ሕትመት ሥራ ግንባር ቀደም እንዲሆኑ ማስቻል በመሆኑ፣ ይህ የልምድ ልውውጥ እና የውይይት መድረክ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ሔኖክ ወልደ ሚካኤል በምርምር ትልመጥናት አዘገጃጀት፣ በምርምር በጀት አፈላለግ፣ በምርምር ሂደት እና በሚያግጥሙ ተግዳሮቶች ዙሪያ ያላቸውን ልምድ ለውይይት መነሻ አድርገው ያቀረቡ ሲሆን፣ ተሳታፊዎችም ጠቃሚ የሆኑ ተሞክሮዎችን ማግኘታቸውን፣ የተገኘውን ልምድ በተግባር ላይ ማዋል፣ ቀጣይ የአተገባበር ስልጠናዎችን እና የግንኙነት መርሐግብሮችን ማመቻቸት እንደሚያስፈልግ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
የልምድ ልውውጡን መድረክ በንግግር የዘጉት የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዘዳንት ዶ/ር አለባቸው ከሚሶ፣ የሴት ተመራማሪዎች ማኅበር መቋቋሙ ትልቅ ስኬት እና ትሩፋት በመሆኑ ሴት መምህራን ከምርምር ተግባር በተጓዳኝ በአመራርነት ረገድ የሚኖራቸውን ድርሻ ማጎልበት ስለሚጠበቅባቸው ዩኒቨርሲቲውም አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *