(ኮትዩ፣ ታህሣሥ 22 ቀን 2018 ዓ.ም) – የኢፌዴሪ የትምህርት ሚንስቴር ሚኒስትር የተከበሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እና የጠቅላይ ሚንስትሩ የማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚንስትር እና የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ የተከበሩ ሙአዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፣ ዩኒቨርሲቲው ተግባራዊ እያደረገው ባለው አጠቃላይ የተቋማዊ ለውጥ አቅጣጫዎች፣ ስትራቴጂዎች እና የለውጥ ተግባራት ዙሪያ ከዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ጋር ውይይት አድርገዋል።
የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ዶ/ር ተሾመ ነቃጥበብ ባደረጉት የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር፣ ዩኒቨርሲቲውን ሞዴልና እውነተኛ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ለማድረግ አዲስ አወቃቀር ከመፍጠርና የኃላፊነት ቦታዎችን በውድድር ከመመደብ በተጨማሪ፣ እንደመርሕ እያንዳንዱ የለውጥ ሥራ የሚከናወነው ግልጽ እና ፍትሐዊ በሆነ የአሠራር መመሪያ መሆኑንና ይህም ጥናትን መሠረት በማድረግ የሚፈጸም መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የለውጥ መነሻችንም ሆነ መድረሻችን ሳይንስ ነው ያሉት ፕሬዘዳንቱ፣ ስለሆነም የለውጥ ሂደቱን ደረጃ በደረጃ ለመተግበር የዩኒቨርሲቲውን ማህበረሰብ ማወያየት፣ የለውጥ ኃይሎችን መመደብና ወደ ሥራ የማስገባት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን በመጥቀስ፣ ይህንን ጨምሮ በለውጡ አቅጣጫ እስካሁን የተከወኑ ተግባራትን ገልጸዋል፡፡
የኢፌዴሪ ትምህርት ሚንስቴር ሚኒስትር የተከበሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፣ ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ቀድሞ ከሚታወቅበት ማንነቱ በላቀ ደረጃ እንዲሠራና በእውቀትም፣ በስነምግባርም የተመሰገኑ፣ በማህበረሰቡ ወስጥ እንደ አርአያ የሚወሰዱ መምህራንን እንዲያፈራ እንደሚፈለግ ገልጸዋል፡፡
አጠቃላይ ሀገራዊ ለውጥ የትምህርት ዘርፉን ጨምሮ በሁሉም ዘርፎች በመካሄድ ላይ መሆኑን የጠቆሙት ክቡር ሚንስትሩ፣ በትምህርቱ ዘርፍ የሚደረገውና በቅርቡ ተግባራዊ የሚሆነው ለውጥም መምህራንን ትርጉም ባለው መልኩ ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን በመግለጽ፣ በኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የሚተገበረው ለውጥም የዚሁ ሀገራዊ ለውጥ አካል መሆኑን ጠቁመዋል።
የጠቅላይ ሚንስትሩ የማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚንስትር እና የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ የተከበሩ ሙአዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በበኩላቸው፣ ኮተቤ በኢትዮጵያ የትምህርት ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ አሻራቸውን ካሳረፉ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መካከል አንዱ መሆኑን ገልጸው፣ ተቋሙ በትምህርቱ ዘርፍ ያለውን ትልቅ ልምድ ከዘመኑ አሠራር እና ለውጥ ጋር አብሮ ማስኬድ ስለሚጠበቅበት ዩኒቨርሲቲው ያቀደውን የለውጥ አሠራር በማሳካት ሀገራዊ ተልዕኮውን እንዲወጣ በትብብር ሠርተን በጋራ እናሳድገዋለን ብለዋል፡፡







