(ኮትዩ፣ ታሕሣሥ 10 ቀን 2018 ዓ.ም) – የዩኒቨርሲቲው የአንደኛ ዓመት ተማሪዎች የአድዋ ድል መታሰቢን እና የሳይንስ ሙዚየምን ጎብኝተዋል፡፡
የአድዋ ድል መታሰቢያ (አድዋ ዜሮ ዜሮ) ሙዚየሙ ከዛሬ 128 ዓመታት በፊት ኢትዮጵያውያን የጣሊያንን ወራሪ ኃይል በህብረት መክተው በማሸነፍ አድዋን የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ድል ምልክት እንዲሆን ያስቻሉ የጦር መሪዎች ስምና ሐውልት፣ የጦርነቱ ተሳታፊዎች እና የተጠቀሙበት የጦር መሣሪያዎች እንዲሁም ልዩ ልዩ ታሪካዊ እውነታዎችን ያካተተ ሲሆን፣ ይህንን እውነታ የሚያሳዩትን ልዩ ልዩ ቅርሶች ተማሪዎቹ ተዟዙረው ጎብኝተዋል፡፡
ቀጥሎ ተማሪዎቹ ያቀኑት በመዲናችን አዲስ አበባ አስደናቂ እና ማራኪ በሆነ የቀለበት እና የጉልላት ቅርጽ ወደ ተገነባው የሳይንስ ሙዚየም ሲሆን፣ በሙዚየሙ የሰውሰራሽ አስተውሎት (አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ)፣ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች፣ የጤና፣ የኢኮኖሚ፣ የግብርና፣ የከተማ፣ የትራንስፖርት፣ የስፔስ ሳይንስና ሌሎች ዘርፎችን በፍጥነት በማሳደግ ሁለንተናዊ የሆነ ሀገራዊ ለውጥና ዕድገት ማምጣት እንደሚቻል በሙዚየሙ አስጎብኚ ለተማሪዎች ሙያዊ ገለጻ ተደርጓል፡፡
በጉብኝቱ የተሳተፉት የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች በሰጡት አስተያየት በተመለከቷቸው ነገሮች እውቀትንና ተሞክሮዎችን መቅሰማቸውን ገልጸው፣ ዩኒቨርሲቲው ይህንን በማዘጋጀቱ አድናቆታቸውን እና ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
ጉብኝቱን በማስተባበር እና በማመቻቸት ረገድ የዩኒቨርሲቲው የተቋማዊ ለውጥ ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት፣ የተማሪዎች አገልግሎት ዲን ቢሮ እና ሌሎች ክፍሎች ተሳትፈዋል፡፡










