ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ከህዳር 2009 ዓ.ም ጀምሮ ዩኒቨርሲቲውን በፕሬዘዳንትነት ሲያገለግሉ የቆዩትን ዶ/ር ብርሃነመስቀል ጠናን አመስግኖ በመሸኘት፣ ለአዲሱ ፕሬዘዳንት ዶ/ር ተሾመ ነቃጥበብ አቀባበል አድርጓል፡፡
በሥነስርዓቱ ላይ በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ የአስተዳደር ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል ዶ/ር ሰለሞን አብርሃ የተገኙ ሲሆን፣ ተሰናባቹ ፕሬዘዳንት ዶ/ር ብርሃነመስቀል ጠና፣ ዩኒቨርሲቲውን ሲመሩ በቆዩባቸው ጊዜያት ያከናወኗቸውን ዋና ዋና ተግባራትና ያጋጠሟቸውን ተግዳሮቶች፣ እንዲሁም በቀጣይ የታቀዱ ተግባራትን በመግለጽ፣ አመራርነት ቅብብሎሽ በመሆኑ አዲሱ ፕሬዘዳንት የተጀመሩትን ተግባራት እንዲያስቀጥሉ አደራ ብለዋል፡፡
አዲሱ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዘዳንት ዶ/ር ተሾመ ነቃጥበብ በበኩላቸው በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ለበርካታ ዓመታት ማገልገላቸውን በመጥቀስ፣ የሀገር ውስጥና ዓለምአቀፍ ልምዳቸውን በመጠቀም የተጣለባቸውን ሀገራዊ ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት እንደሚሠሩ፤ በቀጣይ ጊዜያትም ኮተቤ እንደ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ምንምን ጉዳዮችን አሻሽሎና አካቶ መቀጠል እንዳለበት፣ በሠራተኞችና በአመራሩ መካከል ስለሚኖረው ግንኙነት፣ በአጠቃላይ ዩኒቨርሲቲው ስለሚጓዝባቸው አቅጣጫዎችና አሠራሮች ገለጻ አድርገዋል፡፡
በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ የአስተዳደር ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል ዶ/ር ሰለሞን አብርሃ፣ የዩኒቨርሲቲው ካውንስል አባላት ከአዲሱ ፕሬዘዳንት ጋር በትብብር በመሥራት የዩኒቨርሲቲውን ተልዕኮዎች የማሳካት ተግባራት እንዲያከናውኑ አሳስበው፣ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም ዩኒቨርሲቲው የሚያከናውናቸውን ተግባራት በቅርብ ሆኖ እንደሚደግፍ ገልጸው የቀድሞ ፕሬዘዳንት ዶ/ር ብርሃነመስቀል ጠና ተቋሙን በዚህ ደረጃ ለውጠው ለማሰረከብ ለከፈሉት ዋጋ በትምህርት ሚኒስቴር ስም አመስግነዋል ፣፡
በመጨረሻም የቀድሞው ፕሬዘዳንት ዶ/ር ብርሃነመስቀል ጠና፣ ለአዲሱ ፕሬዘዳንት ዶ/ር ተሾመ ነቃጥበብ የዩኒቨርሲቲውን የ2017 ዓ.ም ሪፖርት፣ የዩኒቨርሲቲውን ፍኖተ ካርታ፣ የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ እና ዩኒቨርሲቲው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የተሰጠውን የማስፋፊያ ቦታ ካርታ አስረክበዋል፡፡