Skip to content

የፀረ-ጾታዊ ጥቃት፣ አካል ጉዳተኞች እና የዓለም ፀረ-ኤድስ ቀን በኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ተከበረ

(ኮትዩ፣ ህዳር 19 ቀን 2018 ዓ.ም) – ዕለቱ የተከበረው ጥቃትን የማይታገስ ማህበረሰብ ለትውልድ ግንባታ፣ አካል ጉዳተኝነትን የሚያካትት ማህበረሰብ መገንባት ለተሻለ ማህበራዊ ዕድገት፣ ተግዳሮቶችን በመቋቋም የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ምላሽን ዘላቂነት እናረጋግጥ በተሰኙ መሪ ቃል ነው፡፡
በበዓሉ ላይ የተገኙት የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ዶ/ር ተሾመ ነቃጥበብ ባሰሙት የመክፈቻ ንግግር፣ በሀገራችን ውስጥ የሁሉንም ዜጎች መብት ከማክበር በተጓዳኝ በተለየ ሁኔታ የሚጎዱ ዜጎችን መብት መጠበቅ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው፣ ከእነዚህም መካከል በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚፈፀም ጉዳትን በእውቀት ላይ በተመሠረተ ስልት መከላከል፣ በህብረተሰቡ ዘንድ መከባበርና መቻቻልን ማስረጽ፣ አካል ጉዳተኞችን ከግምት ውስጥ ያስገቡ አገልግሎቶችን መስጠት፣ አካል ጉዳተኞች አእምሯቸው ምጡቅ ስለሆነ አእምሯቸውን በሁሉም መስክ መጠቀም፣ እነዚህንም ጉዳዮች በዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማር ሂደት የሥራችን አካል አድርገን መንቀሳቀስ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
በኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች አካቶ ትግበራ ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር አልማዝ ደብሩ በየዓመቱ በመድረኩ ላይ የሚነሱ ርዕሰ ጉዳዮች ተመሳሳይነት ያላቸው ቢሆኑም፣ ተግባራዊ ለውጥ ለማምጣት ግን በማህበረሰቡ ዘንድ የሚንጸባረቁ የአመለካከት ችግሮችን መቅረፍ፣ በተማሪዎቻችን ላይ መስራት፣ ሁሉም ወገን የሚጠበቅበትን ድርሻ በቃል ሳይሆን በተግባር መወጣት እንዳለበት አብራርተዋል፡፡
የፀረ-ጾታዊ ጥቃት፣ አካል ጉዳተኞች እና የዓለም ፀረ-ኤድስ ቀንን በተመለከተ መነሻ ሃሳብ ያቀረቡት በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ የአስተዳደር ጉዳዮች ዴስክ ባለሙያ አቶ ተስፋዬ መኮንን፣ ፆታዊ ጥቃትን ለመከላከል፣ አካል ጉዳተኞችን አሳታፊና ተደራሽ ለማድረግ፣ እየተዘነጋ ያለውን የኤች.አይ.ቪ./ኤድስ ስርጭትን ለመከላከል ብሎም የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥና ጤናው የተጠበቀ ብቁ ዜጋ ለማፍራት በሚደረገው ሂደት የዩኒቨርሲቲው አመራር፣ መምህራን፣ ተማሪዎችና የአስተዳደር ሠራተኞች ድርብ ኃላፊነት ያለባቸው መሆኑን አመልክተዋል፡፡
በቀረበው የውይይት መነሻ ሃሳብ ላይ ተሳታፊዎች የተወያዩ ሲሆን፣ የአካል ጉዳተኛ የሆነው ተማሪ ጌታሁን ተገነው ሀገራዊ ጉዳዮችን የተመለከተ ግጥም አቅርቧል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *