(ኮትዩ፣ ህዳር 26 ቀን 2018 ዓ.ም) – የእውቅና ደብዳቤ የተሰጣቸው ተመራማሪዎች በ2018 ዓ.ም የበጀት ዓመት በድጎማ ጥናትና ምርምር (Grant Research)፣ በማህበረሰብ ጉድኝት አገልግሎት እንዲሁም በኢኖቬሽን እና የቴክኖሎጂ ፈጠራ ሽግግር ፕሮጀክት ዙሪያ ምርምር ለማካሄድ ዩኒቨርሲቲው ባወጣው ማስታወቂያ መሠረት ከቀረቡለት ትልመ ጥናቶች ተቀባይነት ላገኙት 70 የጥናት ርዕሶች ነው፡፡
በእውቅና መርሐግብሩ ላይ የተገኙት የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ዶ/ር ተሾመ ነቃጥበብ፣ የምርምር ርዕሶቻችሁ ተቀባይነት አግኝቶ ለማሸነፍ በመቻሉ እንኳን ደስ አላችሁ በማለት ለተመራማሪዎቹ መልካም ምኞታቸውን በመግለጽ፣ የዕለቱ መርሐግብር የምርምር ሥራ እንሰራለን በማለት ቃል የምነገባበት ነው ብለዋል፡፡ ውጤታማ የምርምር ሥራ በመስራት እውቅና ባላቸው ጆርናሎች ላይ ከማሳተም ጎን ለጎን ለምርምር ተግባራቱ ዩኒቨርሲቲው እውቅና እንደሚሰጥና በሂደት የሚያጋጥሙ ችግሮችንም በጋራ ለመፍታት ዝግጁ መሆኑን ፕሬዘዳንቱ ጨምረው ገልጸዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው የምርምርና የማህበረሰብ ጉድኝት ምክትል ፕሬዘዳንት ዶ/ር ቴዎድሮስ ሙሉጌታ በበኩላቸው፣ በዩኒቨርሲቲው ለሚካሄዱት ለእነዚህ ምርምሮች 42.5 ሚሊየን ብር መመደቡን ገልጸው፣ ለዩኒቨርሲቲው ተልዕኮዎች ስኬታማነት ሲባል ምርምሮቹን በተገቢው ጥራት መስራት እንደሚገባ ከአደራ ጋር አሳስበዋል፡፡
በመርሐግብሩ ላይ የምርምር ህትመት ስነምግባር እና ሥርፀት ዳይሬክተር ዶ/ር እስከዳር ተሰማ፣ የማህበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክተር ዶ/ር መርዕድ ቱፋ፣ የኢንዱስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክተር ዶ/ር መልክሙ አፈታ ስለምርምሮቹ አጠቃላይ ይዘት፣ መመዘኛ እና የአፈጻጸም ክትትል በተመለከተ ገለጻ አድርገዋል፡፡







