(ኮትዩ፣ ህዳር 24 ቀን 2018 ዓ.ም)– 20ኛው የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን “ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለኅብረብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ቃል በኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፣ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ ሠራተኞች እና ተማሪዎች በተገኙበት ተከበረ።
ዝግጅቱን በይፋ ያስጀመሩት የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዘዳንት ዶ/ር አለባቸው ከሚሶ፣ “ይህን በዓል ስናከብር የሚያለያዩንን ግድግዳዎች በማፍረስና አንድነታችንን የሚያጠናክሩ ድልድዮችን በመገንባት ይሁን” ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። ዶ/ር አለባቸው አክለውም በብዝሃነትና በኢትዮጵያዊ ማንነት መካከል ተገቢ ሚዛን አስጠብቆ መኖር እንደሚቻል ዩኒቨርሲቲዎች ጥሩ ማሳያዎች መሆናቸውን ገልጸው፣ ዩኒቨርሲቲዎች ኅብረብሄራዊነትን ከብሔራው ማንነት ጋር ሚዛን አስጠብቆ መቀጠል እንደሚቻል የምናስተምርባቸውና የምንመራመርባቸው ተቋማት ናቸው ብለዋል።
በዝግቱ ላይ የተገኙት በአዲስ አበባ ከተማ የየካ ክ/ከተማ ዋና አፈ ጉባኤ አቶ ብስራት ማጆሬ በበኩላቸው፣ ኅብረበሔራዊ ማንነታችን ልዩነቶቻችንን ከማስፋፊያነት ይልቅ የጋራ ጉዳዮቻችን ላይ በማተኮር ለሀገራዊ አንድነት መስራት ይገባል ብለዋል።
አቶ ሄኖክ አሰፋ በየካ ክፍለ ከተማ የፐብሊክ ሰርቪስ ሰው ሀብት ልማት ጽ/ቤት የሪፎርም ክትትልና ድጋፍ ቡድን መሪ “ዴሞክራሲ እና የፌዴራል ሥርዓት በኢትዮጵያ፤ ተስፋዎቹና ስጋቶቹ” በሚል ርዕስ ጽሑፍ አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል።









