የኢትዮጵያ የባህል ስፖርቶችን እንደሚያሳድግ የታመነበት ስምምነት ተፈረመ፡፡

የኢትዮጵያ የባህል ስፖርቶችን እንደሚያሳድግ የታመነበት የሁለትዮሽ ስምምነት ዛሬ ሚያዚያ 13 ቀን 2017 ዓ.ም በኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ እና በኢትዮጵያ የባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን መካከል በካፒታል ሆቴል ተፈርሟል፡፡ ስምምነቱ ጥናትና ምርምሮችን፣ የትምህርት እና የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን እንዲሁም ተያያዥ ጉዳዮችን በጋራ መስራትን ዓላማው ያደረገ ሲሆን፣ በዚህም የኢትዮጵያ የባህል ስፖርቶችን በሀገር ውስጥና በዓለምአቀፍ ደረጃ ተወዳጅና ተዘውታሪ የውድድር መስክ እንዲሆን ማስቻልን ግቡ እንዳደረገ በመድረኩ ተገልጿል፡፡
በኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ በኩል የዩኒቨርሲቲውን ፕሬዚዳንቱን ወክለው ስምምነቱን የፈረሙት የዩነቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ፕሬዘዳንት ዶ/ር ፈቀደ ቱሊ፣ ሀገራችን የብዝሐ ባህል ባለቤት ብትሆንም፣ የባህል ስፖርቶቻችን መታወቅ በሚገባቸው ልክ ያልታወቁና ያልለሙ በመሆኑ ይህን ክፍተት ለመሙላት በየአካባቢው ያሉትን የባህል ስፖርቶች ለማጥናት እና ለማሳደግ በስፖርት ሳይንስ ዘርፍ ግንባር ቀደም የሆነው የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ከኢትዮጵያ የባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር ለመስራት ዝግጁ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
የኢትዮጵያ የባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ፕሬዘዳንት ወ/ሮ ህይወት መሐመድ፣ የዘመናዊ ስፖርቶች መነሻ ባህላዊ ስፖርቶች በመሆናቸው፤ የሀገራችንን የባህል ስፖርቶች በማጥናት፣ ወደ ውድድር እንዲገቡ በማድረግ፣ አሁን ውድድር እየተካሄደባቸው ያሉትንም የኢትዮጵያ የባህል ስፖርቶች በዓለምአቀፍ ደረጃ በማስተዋወቅና በማስፋፋት ረገድ ከአንጋፋው የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ ለመስራት የሁለትዮሽ የአጋርነት ስምምነት በመፈራረማቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
በሥነስርዓቱ ላይ የተገኙት የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እና የፌዴሬሽኑ የሥራ አስፈጻሚ አባላትም በበኩላቸው፣ ለሁለትዮሽ የአጋርነት ስምምነቱ ተፈጻሚነት እና ውጤታማነት በትጋት በመሥራት ረገድ ያላቸውን ቁርጠኝነት ገልጸዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *