ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ በሳይንስ ሼርድ ካምፓሱ ላለፉት አራት ዓመታት ሲያስተምራቸው የቆዩትን የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎቹን ነሀሴ 17 ቀን 2017 ዓ.ም ዕውቅና ሰጥቷል።
የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ሳይንስ ሼርድ ካምፓስ፣ በአዲስ አበባ ከተማ እና በከተማዋ ዙሪያ የሚገኙ፣ በ8ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ፣ ከፍተኛ የሳይንስ ክህሎት ያላቸውን ተማሪዎች ተቀብሎ የሚያስተምር መሆኑን የገለጹት የካምፓሱ ዲን ዶ/ር ቴዎድሮስ፣ የዚህ ዓመት ተመራቂ ተማሪዎችም ሰባተኛ ዙር መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
በዕውቅና ሥነስርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ዶ/ር ብርሃነመስቀል ጠና፣ እናንተ የዛሬ ተመራቂ ተማሪዎች ትውልድን ከታች ይዞ በመኮትኮት ለውጤት ማብቃት እንደሚቻል ማሳያ ናችሁ፤ ስለጉብዝናችሁም ምስክርነትን እሰጣለሁ ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ በቀጣይ በሚኖራችሁ የዩኒቨርሲቲ ቆይታም እንደቀደምቶቻችሁ ሁሉ በትምህርታችሁ የላቀ ውጤት በማምጣት በየዩኒቨርሲቲያችሁ ተሸላሚና የሀገር ተስፋ መሆን አለባችሁ ያሉ ሲሆን፣ ለዚህም ተማሪዎች ራሳቸውን ከማንም ጋር ሳይሆን ከራሳቸው ጋር ብቻ ሊያወዳድሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ተማሪዎቹ ዩኒቨርሲቲው ላደረገላቸው በተለይም የዩኒቨርሲቲው ፕሬዘዳንት ዶ/ር ብርሃነመስቀል ጠና ሲያደርጉላቸው ለነበረው አባታዊ እንክብካቤና ክትትል ምስጋናቸውን የገለጹ ሲሆን፣ በተወካዮቻቸው አማካይነትም የማስታወሻ ስጦታ አበርክተውላቸዋል፡፡