የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ አዲሱ ፕሬዘዳንት ዶ/ር ተሾመ ነቃጥበብ ከሁሉም ኮሌጆች መምህራን ጋር ለመተዋወቅና በዩኒቨርሲቲው አጠቃላይ አሠራሮች ላይ ውይይት ለማድረግ በተያዘው መርሐግብር መሠረት ከዩኒቨርሲቲው ስድስት ኮሌጆች ዲኖች፣ የትምህርት ክፍል ኃላፊዎች እና መምህራን ጋር ለሁለት ቀናት ውይይት አድርገዋል።
ዶ/ር ተሾመ ነቃጥበብ በስነትምህርት እና ተያያዥ መስኮች የሀገር ውስጥ እና ዓለምአቀፍ ልምዳቸውን በማውሳት ራሳቸውን ያስተዋወቁ ሲሆን፣ ዩኒቨርሲቲው እንደ ትምህርት ዩኒቨርሲቲነቱ በቀጣይ ትኩረት ሰጥቶ ስለሚያሻሽላቸው የመማር ማስተማር፣ የምርምር፣ የዕውቀት ማሻሻልና መጠበቅ፣ የፕሮግራሞች አሰጣጥና አቀራረጽ፣ ተቋማዊ መልካም ግንኙነት፣ በሠራተኞች መካከል መኖር ስለሚገባው መልካም የእርስበርስ ግንኙት፣ ተቋማዊ ራዕይ እና ተቋማዊ ገቢ ማመንጨት ጉዳዮች ላይ ገለጻ አድርገዋል፡፡
በውይይቱ የተሳተፉት መምህራን በበኩላቸው ባለፉት ዓመታት በዩኒቨርሲቲው በየዘርፉ ትልልቅ ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸው፣ በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሠራባቸው ይገባል ያሏቸውን ክፍተቶች በመድረኩ አንስተዋል፡፡