Skip to content

በዘንድሮው የዩኒቨርሲቲዎች የስፖርት ፌስቲቫል ላይ ለሚሳተፈው የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ልዑክ አሸኛኘት ተደረገ

(ኮትዩ፣ ጥር 14 ቀን 2018 ዓ.ም)- በጅማ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት በሚካሄደው የ2018 ዓ.ም የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች የስፖርት ፌስቲቫል ላይ ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲን ወክለው ለሚሳተፉ የስፖርት ልዑካን አባላት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዘዳንት፣ ምክትል ፕሬዝዳንቶች እና የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ደማቅ የአሸኛኘት ሥነስርዓት ተከናውኗል።
የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ዶ/ር ተሾመ ነቃጥበብ ባሰሙት የሽኝትና የአደራ ቃል፣ የስፖርት ውድድር ብቃትንና ጉብዝናን እንዲሁም ማሸነፍ መቻልን የምናሳይበት መድረክ መሆኑን ገልጸው፣ ዩኒቨርሲቲው የምስጉን የትምህርት ባለሙያዎች መፍለቂያ በመሆኑ ተማሪዎቻችን፣ ሌሎች ከእነርሱ እንዲማሩ ምሳሌ መሆን እንዳለባቸውና በውጤት ለሽልማት መብቃትና ተቋሙን እና የተቋሙን ማኅበረሰብ ማኩራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ፕሬዘዳንቱ በንግግራቸው የስፖርት ልዑካን ቡድኑ ከውጤት ባሻገር በዲሲፕሊን ምስጉን መሆን እንዳለበትም አሳስበዋል።
በአሸኛኘት ሥነስርዓቱ ላይ የተገኙት የዩኒቨርሲቲው ሌሎች የሥራ ኃላፊዎችም ለልዑካን ቡድኑ የመልካም ምኞት መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን፣ ተማሪዎቹም በበኩላቸው በውድድሩ ጥሩ ውጤት በማምጣት የዩኒቨርሲቲውን ስም ለማስጠራት ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል።
የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ልዑካን ቡድን በዘንድሮው ፌስቲቫል በ11 የስፖርት ዓይነቶች እንደሚሳተፍ ለማወቅ ተችሏል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *