(ጅማ፣ ጥር 17 ቀን 2018 ዓ.ም) – 49 ዩኒቨርሲቲዎች የሚሳተፉበትና በጅማ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት የሚካሄደው የዘንድሮው የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የተማሪዎች የስፖርት ውድድርና ፌስቲቫል የመክፈቻ ሥነስርዓት ላይ የባህልና ስፖርት ሚንስትር ዴኤታ አቶ መኪዩ መሐመድ፣ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች የስፖርት ማኅበር ፕሬዘዳንት አቶ አባይ በላይሁን፣ የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ዶ/ር ተሾመ ነቃጥበብ እና የሌሎችም ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዘዳንቶች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የክብር እንግዳው የባህልና ስፖርት ሚንስትር ዴኤታ አቶ መኪዩ መሐመድ ባሰሙት ንግግር፣ የኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተማሪዎች የስፖርት ውድድር እና ፌስቲቫል በዩኒቨርሲቲዎች መካከል መቀራረብን እንዲኖር ከማስቻሉም በተጨማሪ፣ ለመማር ማስተማር ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ብለዋል፡፡
በጅማ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት ከዛሬ ጀምሮ ለ15 ተከታታይ ቀናት፣ በወንድና ሴት ፆታዎች በ15 የስፖርት ዓይነቶች ውድድሮች ይካሄዳሉ።
ስፖርታዊ ውድድሩ በውጤት ከማሸነፍና ከመሸነፍ ባሻገር ለእርስ በርስ ትውውቅና መቀራረብ፣ ለብዝሐነት መስተጋብር እና ለባህል ልውውጥ፣ ብሎም ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ተገልጿል።










