መምህራን ጊዜውን በሚመጥን ክህሎት፣ ዕውቀትና አመለካከት የታነፁ መሆን እንዳለባቸው ተገለጸ፡፡

የመማር ማስተማር ሂደትን ፣ የምርምር እና የማህበረሰብ አገልግሎትን በተመለከተ ከኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ መምህራን ጋር በ04/03/2017 ዓ.ም በተደረገው ውይይት የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዘዳንት ዶ/ር ፈቀደ ቱሊ ባቀረቡት የውይይት መነሻ ሐሳብ፣ በዓለምዓቀፍ ደረጃ የሚታየው ለውጥ ፈጣን በመሆኑ መምህራን ጊዜውን የሚመጥን ክህሎት፣ ዕውቀትና አመለካከት እንዲኖራቸው ራሳቸውን በየጊዜው ማዘጋጀት እንዳለባቸው ገለጸዋል፡፡
ለውጤታማ የመማር ማስተማር ሂደት መምህራን ሁልጊዜም ማንበብና ምርምር ማካሄድ እንዳለባቸው ያሳሰቡት ዶ/ር ፈቀደ፣ የመመረቂያ ጽሑፍ የሚያማክሩ መምህራን ለራሳቸውም በምርምር ተግባር ውስጥ ያሉ መሆን እንደሚገባቸውና ለተማሪዎቻቸው ያማከሩትንም ሃሳብ መሰነድ እንዳለባቸው፣ ይህም በየጊዜው እየተገመገመና እየዳበረ መሄድ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
በኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ “በብቁ መምህራን ብቁ ትምህርት ለትምህርት ጥራት ” በሚል ዩኒቨርሲቲው የነደፈው በየሳምንቱ ረቡዕ ጠዋት በመማር ማስተማር፣ በጥናትና ምርምር ፣ በማህበረሰብ አገልግሎት እንዲሁም ከሥርዓተ ትምህርት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ያተኮረው ሳምንታዊ Learning Forum ተጠናክሮ ቀጥሏል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *