(ኮትዩ፣ መጋቢት 3 ቀን 2018 ዓ.ም) – ዓለምአቀፍ የሴቶች ቀን (ማርች 8 በኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ተከብሯል፡፡
በመድረኩ የእንኳን ደህና መጣችሁ እና የእንኳን ደስ ያላችሁ ንግግር ያሰሙት የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ዶ/ር ተሾመ ነቃጥበብ፣ “በዓለምአቀፍ ደረጃ ለ115ኛ ጊዜ፣ በሀገራችን ደግሞ ለ50ኛ ጊዜ “50 ዓመት የሴቶች ድምጽ ለእኩልነት እና ለበለጸገች ኢትዮጵያ” በሚል መሪ ቃል የሚከበረው ዓለምአቀፍ የሴቶች ቀን፣ ሴቶች በማኅበረሰብ፣ በትምህርት፣ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ እና በልማት ዘርፎች ያበረከቱትን አስተዋፅኦ፣ ይልቁንም በቀጣይ የሚያከናውኗቸውን ታላላቅ ተግባራት የምንዘክርበት ቀን ነው” ብለዋል፡፡ በዚህ ረገድ ዩኒቨርሲቲው ሴቶች በምርምር፣ በማስተማር እና በአመራርነት ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ ትኩረት ሰጥቶ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ መሆኑን የገለጹት ፕሬዘዳንቱ፣ ይህንንም ጥረት በቀጣይም አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
በበዓሉ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የኢፌዴሪ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሸዊት ሻንካ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር፣ “ዓለምአቀፍ የሴቶች ቀን (ማርች 8 ለእኛ ለሴቶች ትርጉሙ ጥልቅ ነው፤ ይህም የሆነበት ምክንያት በታሪክ ውስጥ ሴቶች ወደ ትምህርት ገበታና ወደ ጥናትና ምርምር አዳራሾች እንዳይገቡ በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫናዎች ተከልክለው ከነበረበት ዘመን ወጥተው ለዛሬው ማንነታችን መሠረት የተጣለበት፤ የእናቶቻችን ጽናት ፍሬ አፍርቶ ውጤት የታየበት ዕለት በመሆኑ ነው” ብለዋል።
“ዛሬ በዚህ አዳራሽ የተሰበሰብነው በዓሉን ለመዘከር ብቻ ሳይሆን ባለፉት አምስት አስርት ዓመታት ውስጥ lሴት ምሁራን በሀገራችን የተፈጠረውን ጉልህ ለውጥና እድገት እንዲሁም ታሪካዊ ጉዞዎችን እውቅና ለመስጠት ጭምር ነው” ያሉት ሚኒስትሯ፣ በዓሉ በዓለምአቀፍ ደረጃ ሴቶች በሳይንስ፣ በቴክኖሎጅና በፖሊሲ ቀረጻ ዘርፍ ያላቸውን እምቅ አቅም በተግባር ያሳዩበት፣ እውቀት ጾታ እንደማይለይ ለዓለም ያረጋገጡበት፤ የሴቶች ጉዞ የሚታወስበት ታላቅ መድረክ መሆኑንም አውስተዋል።
የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የሴት ተመራማሪዎች ማኅበር ፕሬዘዳንት ዶ/ር አልማዝ ደብሩ “የኢትዮጵያ ሴቶች ምሁራን ያበረከቱት አስተዋፅኦና ያጋጠሟቸው ተግዳሮቶች”፤ እንዲሁም በዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች ስብዕና ግንባታ ምክትል ዲን ወ/ሮ ምኞት ጌታቸው፣ “የ50 ዓመታት የለውጥ ጉዞ እና የማርች 8 ታሪካዊ ፋይዳ” በሚሉ ርዕሶች በሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የተዘጋጁ ሁለት የመወያያ ሰነዶችን በማቅረብ ውይይት ተካሂዷል፡፡
በውይይቱም የሴቶች ሁለንተናዊ ሀገራዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ከቀደመው ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩ፣ በቀጣይም የተገኘውን ውጤት አጠናክሮ መቀጠል፣ ለዚህም በመድረኩ የተነሱ ሃሳቦችን በተግባር ወደ ውጤት መቀየር፣ ለተፈጻሚነቱም የወንዶችን አጋርነት በአወንታዊ አመለካከት ማጎልበት እና ሴት ምሁራን ትስስር በመፍጠር የግንባር ቀደምትነት ሚና መጫወት እንደሚጠበቅባቸው ከመግባባት ላይ የተደርሷል፡፡
በዩኒቨርሲቲው በልዩ ልዩ ዝግጅቶች በተከበረው በዚህ በዓል ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶች፤ ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ክብርት ወ/ሮ ቆንጂት ደበላ፣ የኢትዮጵያ ኢንቨሰትመት ሆልዲንግ ምክትል ዳይሬክተር ክብርት መልዕክተ ሳህሉ፣ የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳዮች አካቶ ትግበራ ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ፋሲካ በላይ እና ከተለያዩ የመንግሥት ተቋማት የመጡ እንግዶች ሃሳባቸውን አካፍለዋል፡፡







