Skip to content

የዩኒቨርሲቲው ማኔጅመት በአዲሱ የአካዳሚክ ፕሮግራም ሪፎርም ረቂቅ ላይ የዩኒቨርሲቲውን መምህራን አወያየ

(ኮትዩ፣ ግንቦት 7 ቀን 2018 ዓ.ም) – የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ከሚቀጥለው አዲስ ዓመት ጀምሮ በተግባር ላይ ሊያውለው ባቀደው የአካዳሚክ ፕሮግራም ሪፎርም እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የተደረገውን ሰፊ ውይይት በንግግር የከፈቱት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዘዳንት ዶ/ር ተሾመ ነቃጥበብ፣ የዚህ ዓይነት ውይይት ዩኒቨርሲቲው የሚሠራቸው ሥራዎች ግልጽነትና አሳታፊነት እንዲኖራቸው ከማስቻሉም በተጨማሪ፣ በሂደት የተስተዋሉ ክፍተቶችን ለማረም ዕድል የሚያመቻች በመሆኑ ጠቃሚ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው በበርካታ ዛርፎች ላይ ወሳኝ የሚባል ሪፎርሞች እያካሄደ እያካሄደ መሆኑን የጠቀሱት ፕሬዘዳንቱ፣ ከእነዚህም አንዱና ዋነኛው የአካዳሚክ ፕሮግራም ሪፎርም መሆኑን በመግለጽ፣ በእስካሁኑ ሂደት የተሠሩ ሥራዎችን በተመለከተ አጠቃላይ በሆነ መልኩ ለውይይቱ ተሳታፊ መምህራኑ አውስተዋል፡፡
አዲሱ ማኔጅመንት ሥራውን ከጀመረ ጊዜ አንስቶ አንድ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ምን መምሰል አለበት የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ሢሰራ መቆየቱን የገለጹት ፕሬዘዳንቱ፣ ዩኒቨርሲቲውን ተልዕኮውን እንዲያሳካ ለማድረግ ሪፎርሙ ያስፈለገ በመሆኑ ማስተማር፣ ዓለምአቀፋዊነት፣ የተማሪ ቅበላ፣ መሠረተ ልማት እና የአካዳሚክ ፕሮግራም ማሻሻያዎች የለውጡ አካል ስለሆኑ ይህን ሪፎርም የሚመራ አካልም በውድድር ለመሰየም መቻሉን አስረድተዋል፡፡ በአስተዳደር ዘርፍም ተመሳሳይ የለውጥ ሥራዎች እየተሠሩ ከመሆናቸውንም በተጨማሪ ከመማር ማስተማሩ ሂደት ጋር የሚጣጣሙ አዳዲስ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች እንደሚካሄዱም አብራርተዋል፡፡
የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዘዳንት ዶ/ር አለባቸው ከሚሶ የአካዳሚክ ፕሮግራም ሪፎርሙ ከጅምሩ አሁን ለውይይት እስከቀረበበት ጊዜ ያለፈበትን በርካታ ደረጃዎች፣ የተሳተፉበትን አካላት፣ የተሠሩትን እጅግ በርካታ እና ዝርዝር ተግባራት በመግለጽ በመጨረሻም በተደረሰበት ግኝት መሠረት፣ አብዛኛዎቹን የአካዳሚክ ፕሮግራሞች ከዩኒቨርሲቲው ተልዕኮ ጋር ለማጣጣም ሲባል የመከለስ፣ ተመሳሳይ የሆኑትን ፕሮግራሞች የማጣማር፣ ከዩኒቨርሲቲው ተልዕኮ ጋር የማይዛመዱ ፕሮግራሞችን ደግሞ እንዲቀነሱ የማድረግ ሥራዎች መሠራታቸውን ማሳያዎችን በማንሳት አቅርበዋል፡፡
የአስተዳደርና ልማት ምክትል ፕሬዘዳንት ዶ/ር ሽመልስ ዘውዴ በኤች፣አይ.ቪ/ኤድስ ፈንድ የኦዲት ግኝቶች ላይ ሪፖርት፣ የተከታታይ ትምህርት ፕሮግራም ክፍያን እና ወጪዎችን አበተመለከተ የአካዳሚክ ፕሮግራም ዳይሬክተር ዶ/ር ዘለቀ ቢዬሮ ገለጻዎችን አቅርበዋል፡፡
የቀረቡትን ገለጻዎች ተከትሎ በተደረገው ውይይት፣ የቀረበው የአካዳሚክ ፕሮግራም ሪፎርም እና የለውጥ ሽግግር ረቂቅ ዩኒቨርሲቲው በቀጣይ ምን መምሰል እንዳለበት በጥልቀት ያሳየ መሆኑ በመምህራን የተገለጸና አድናቆት የተቸረው ሲሆን፣ በውይይቱ መዝጊያም ላይ የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ዶ/ር ተሾመ ነቃጥበብ፣ የአካዳሚክ ፕሮግራሙ ሪፎርም በየደረጃው የተለያዩ ማሻሻያ ተደርገውበት ከመጪው ዓመት መስከረም ወር ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆንና ለተግባራዊነቱም መምህራን የበኩላቸውን እገዛ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *