(ኮትዩ፣ ዿግሜ 1 ቀን 2018 ዓ.ም) – በኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ከነሐሴ 26 እስከ ዿግሜ 01/2018 ዓ.ም ድረስ ሲሰጥ የቆየው የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን የአሰልጣኝነት ሙያ ማሻሻያ ስልጠና ለሰልጣኖች ሰርተፍኬት በመስጠት ተጠናቋል፡፡
በመዝጊያ ሥነስርዓቱ ላይ የተገኙት የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት መሪ ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር አበባ አማረ ለሰልጣኞች ሰርተፍኬት ከሰጡ በኋላ እንደተናገሩት፣ ወርልድ ቴኳንዶ እጅግ ተወዳጅ የስፖርት ዓይነት በመሆኑ፣ የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶን ለመጠበቅ፣ በሂደት የሚገጥሙትን ችግሮች በመፍታት ለማሳደግ ሁላችንም እጅ ለእጅ ተያይዘን በጋራ መስራት የሚያስፈልግ መሆኑን በመግለፅ፣ ሰልጣኞች ስልጠናችሁን ስኬታማ በሆነ መልኩ በማጠናቀቃችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡
የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የሰውነት ማጎልመሻና ስፖርት ኢንስቲትዩት ዲን ዶ/ር ጥላሁን በረደድ በበኩላቸው፣ ትምህርትና ስልጠና የዩኒቨርሲቲያችን ዋና ተግባር በመሆኑ በቀጣይም ተመሳሳይ ስልጠናዎችን በማዘጋጀትና የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን ባለሙያዎችን በማብቃት የስፖርት ዘርፉ ዓለምአቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆን ከማድረግ በተጨማሪ ቴኳንዶ ትውልዱን በስነምግባር እንዲያንፅ ለማድረግ በተጀመረው አግባብ በትብብር እንሠራለን ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን ዋና ጸሐፊ ማስተር ሞቱማ ጌታቸው፣ ወርልድ ቴኳንዶን በሀገር አቀፍ ደረጃ ለማሳደግና ብቃት ያላቸውን ባለሙያዎች ለማፍራት በዲፕሎማና በዲግሪ ደረጃ ትምህርት እንዲሰጥ፣ ባለሙያዎችን ከማብቃት ጎን ለጎን ቴኳንዶንም በየተቋማቱና በየትምህርት ቤቱ እንዲተዋወቅና እንዲስፋፋ፣ እንደሌላው የስፖርት አይነት የተለያዩ ውድድሮችም እንዲዘጋጁ ተከታታይ ስራዎች እንደሚሰሩ በማመልከት ይህ ስልጠና የተሳካ እንዲሆን ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ለነበረው ድርሻ አመስግነዋል፡፡
በስልጠናው ላይ የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን ሥራ አስፈፃሚዎች፣ አሰልጣኞች እና ሰልጣኞች በሰጡት አስተያየት፣ ከኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የተዘጋጀው ይህ ስልጠና በእጅጉ ጠቃሚ በመሆኑ፣ በቀጣይም ከዘመኑ ሳይንስ ጋር በማስተሳሰር መቀጠል አለበት ብለዋል፡፡
– የህዝብ እና ዓለምአቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት
