(ኮትዩ፣ ጥቅምት 22 ቀን 2018 ዓ.ም)- ኮተቤ የትምርት ዩኒቨርሲቲ edify ከተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር በመተባበር የሙያ ማሻሻያ ስልጠና የሰጣቸውን 91 የግል ት/ቤቶች መምህራንን በሰርተፍኬት በዩኒቨርሲቲው የስብሰባ አዳራሽ አስመርቋል፡፡
በምረቃ ምርሐግብሩ ላይ የተገኙት በኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የምርምር እና ማህበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዘዳንት ዶ/ር ኤፍሬም ተክሌ ለተመራቂዎቹ እንኳን ደስ አላችሁ በማለት፣ ለትምህርት ጥራት ችግር የመምህራን የተነሳሽነት ጉድለት ዋነኛ ምክንያት በመሆኑ ይህ ዓይነቱ የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና በዘርፉ የታየውን ክፍተት ለመሙላት እና የትምህርት ጥራትን ለማምጣት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል፡፡
የedify ዓለምአቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክትር አቶ ዘካርያስ ንጋቱ በበኩላቸው በዝቅተኛ የትምህርት ክፍያ የሚያስተምሩ የግል ትምህርት ቤቶችን ለማገዝ ያቀረብነውን ሃሳብ፣ ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ እና የሸገር ከተማ አስተደዳደር ትምህርት ጽ/ቤት ሃሳቡን ከመቀበል ባሻገር መምህራኑን በትብብር በማሰልጠን ለምረቃ ስላበቁ አመስግነዋል፡፡
የሸገር ከተማ አስተደዳደር ትምህርት ጽ/ቤት ምክትል ኃላፊ ዶ/ር ዘሪሁን ታከለ እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ታረቀኝ ወልደሐና ስልጠናው በግል ትምህርት ቤቶች የሚታየውን የፔዳጎጂ፣ የመምህርነት ሙያ ስልጠናና መሰል ችግሮችን በምቀረፍ የመምህራኑን ሙያ በማሻሻል ረገድ ትልቅ ድርሻ ስላለው ተመራቂዎችን እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡
በኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የህይወት ዘመን ትምህርት ዳይሬክተር ዶ/ር ኢዩኤል አባተ ዩኒቨርሲቲው edify ከተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር በመተባበር ለስድስት ወራት ተከታታይ የመምህርነት ሙያ ማሻሻያ ስልጠና ለመውሰድ ተመዝግበው የነበሩት 200 የግል ትምህርት ቤቶች መምህራን መሆናቸውን አስታውሰው፣ ከእነዚህ ውስጥ ተገቢውን መስፈርት አሟልተው የተመረቁት 91 መሆናቸውን እና በስልጠናውም ለመማር ማስተማር ሂደት ግብዓት የሚሆኑ አዳዲስ አሰራሮችን ለማስጨበጥ መቻሉን አብራርተዋል፡፡








