(ኮትዩ፣ ነሐሴ 13 ቀን 2018 ዓ.ም) – የዩኒቨርሲቲው የሥርዓተ ትምህርት ግምገማ በተጀመረበት ወቅት የሥራ አቅጣጫ እና መመሪያ የሰጡት የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ዶ/ር ተሾመ ነቃጥበብ፣ የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ፕሮግራም ክለሳ እና ግምገማ መርሐግብር እንዲሳካ ያደረጉ አካላትን አመስግነው፣ ዩኒቨርሲቲው ከመንግስት በተሰጠው ተልዕኮ መሠረት በለውጥ ውስጥ መሆኑን እና እየተከናወኑ ካሉ የለውጥ ሥራዎች መካከልም በመማር ማስተማር ረገድ እየተካሄደ ያለው የሥርዓተ ትምህርት ማሻሻያ አንዱና ዋነኛው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ቀደም ሲል በነበረው አሠራር በሥርዓተ ትምህርቱ እና የመምህራን ስልጠና ተግባራዊ ሂደት መካከል መራራቅ የነበረ መሆኑንና ይህም የጥራት መጓደል እንዲፈጠር ምክንያት መሆኑን ያነሱት ፕሬዘዳንቱ፣ ይህም የሥርዓተ ትምህርት ለውጥ ለማድረግ ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል። በማሻሻያውም በሁለቱ መካከል ጥብቅ ትስስር ለመፍጠር፣ የትምህርት ሥርዓቱን የሚመሩ አካላት እንዲሁም የምናሰለጥናቸው መምህራን ብቁ ሆነው እንዲገኙ እና አጠቃላይ የትምህርት ጥራትን እውን ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቷል ብለዋል፡፡
እንደ ፕሬዘዳንቱ ገለጻ፣ ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ከመማር ማስተማር ባሻገር ሁሉን ዓቀፍ የምርምር፣ የማኅበረሰብ አገልግሎት፣ የልዩ ልዩ መሠረተ ልማት ግንባታዎችን እና ሌሎች የለውጥ ሥራዎችንም በማከናወን ላይ ሲሆን፣ በዚህ የሥርዓተ ትምህርት ግምገማ ላይ የሚሳተፉ ምሁራን፣ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ ዲኖች፣ ዳይሬክተሮች፣ የትምህርት ክፍል ኃላፊዎች እና መምህራን ውጤታማ ሥራ በመሥራት ዩኒቨርሲተውን ወደተሻለ ደረጃ እንዲያሸጋግሩ አደራ ጨምረው አሳስበዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው የምርምርና የማኅበረሰብ ጉድኝት ምክትል ፕሬዘዳንት ዶ/ር ቴዎድሮስ ሙሉጌታ በበኩላቸው፣ የሥርዓተ ትምህርት ማሻሻያ ሃሳቡን የጠነሰሱ፣ ያጎለበቱ እና የመሩ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ ዲኖች፣ የትምህርት ክፍል ኃላፊዎች እና ሥራውን ሠርተው ያቀረቡ የዩኒቨርሲቲው መምህራን እና ገምጋሚዎችን አመስግነው፣ አጠቃላይ የሥርዓተ ትምህርት ለውጡ እንደ ሀገር የተሰጠንን ኃላፊነት ለመወጣት፣ ፕሮግራሞቻችንን ሳቢ ለማድረግ፣ ብቁ ዜጋ ለማፍራት የሚረዳ በመሆኑ፣ ከመድረኩ ትልቅ ግብዓት እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
የአካዳሚክ ፕሮግራሞች ዳይሬክተር ዶ/ር ዘለቀ ቢዬሮ በመጀመሪያ፣ በሁለተኛና በሦስተኛ ዲግሪ በአጠቃላይ 88 ፕሮግራሞች ለግምገማ መቅረባቸውን በመጥቀስ፣ እነዚህም ፕሮግራሞች የዩኒቨርሲተውን ትኩረት የሚቀይሩ በመሆናቸው ትልቅ ስኬት ነው መሆኑን ብለዋል፡፡
በመርሐግብሩ መሠረት በዛሬው ዕለት የሥነትምህርት ኮሌጅ እና የቋንቋዎች ትምህርት ኮሌጅ የሥርዓተ ትምህርት ግምገማ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በመጡ ገምጋሚዎች የተጀመረ ሲሆን፣ በተለያዩ የትምህርት ፕሮግራሞች ላይ የሚካሄደው ይህ የሥርዓተ ትምህርት ግምገማ ለአራት ተከታታይ ቀናት የሚካሄድ ይሆናል፡፡

– የህዝብ እና ዓለምአቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት

#Kotebe_University_ofEducation_committed_to_excellence_in_Education