የዩኒቨርሲቲውን ሰላማዊ የመማር መስተማር ሂደት ለማስቀጠል በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ውይይት ተካሄደ

(ኮትዩ፣ ነሐሴ 28 ቀን 2018 ዓ.ም) – የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የሰላምና ደህንነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት የ2019 ዓ.ም የሥራ ዕቅድን በተመለከተ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ እና ከዩኒቨርሲቲው ውጪ በአካባቢው ከሚገኙ የፀጥታ አካላት ጋር ባደረገው ውይይት የዩኒቨርሲቲውን የመማር ማስተማር ሂደት የተሻለ፣ ሰላማዊና ምቹ ለማድረግ ቅንጅታዊ ሥራ ለመሥራት ከስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የካምፓስ ፖሊስና የፌዴራል ፖሊስ፣ የተማሪዎች ዲን ጽ/ቤት፣ የወረዳ 11 የፀጥታ ዘርፍ፣ የወረዳ 11 የአካባቢ ፖሊስ ጣቢያ፣ የደንብ ማስከበር እና የወረዳ 12 የአካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ተወካዮች በተሳተፉበት በዚሁ የውይይት መድረክ ላይ፣ የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የሰላምና ደህንነት ሥራ አስፈፃሚ ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኮማንደር አብዲሳ ባይሳ የ2018 ዓ.ም የሥራ አፈጻጻም ውጤታማ እንደነበር ጠቅሰው፣ የዩኒቨርሲቲውን ሰላም አስተማማኝ በሆነ ደረጃ ከማስጠበቅ በተጨማሪ በዩኒቨርሲቲው አካባቢም ተመሳሳይ ሰላምን ለማስፈን ቅንጅታዊ ሥራውና ውይይቱ አስፈላጊ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

የአዲስ ገቢ ተማሪዎች ቅበላ፣ በዩኒቨርሲቲው እየተገነቡ ያሉ ግንባታዎችን ደህንነት መጠበቅ፣ ልዩ ልዩ አጫጭር ስልጠናዎችን ማካሄድ፣ የተማሪዎችን የትምህርት ሂደት የሚጎዱ እንደ ጫት ቤት፣ ሺሻ ቤት፣ የመጠጥና የአደገኛ ዕፆች እና ከረንቡላ ቤቶች ላይ አስፈላጊውን ቁጥጥር ማካሄድ፣ የዩኒቨርሲቲውን ማህበረሰብ ያሳተፈ የሰላምና ደህንነት ሥራዎችን መስራት የመሳሰሉት ከአዲሱ ዓመት ዋና ዋና ዕቅዶች መካከል የሚመደቡ መሆናቸውን ኮማንደር አብዲሳ ባይሳ አብራርተዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የሰላምና ደህንነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት የመረጃና ደህንነት ቡድን መሪ ኮማንደር በየነ ዱሬሳ በበኩላቸው፣ የ20019 ዓ.ም ዕቅድ በዋናነት የተዘጋጀው በአዲሱ ዓመት አዲስ ተማሪዎች ከመግባታቸው በፊት የጥምር ኮሚቴው ዝግጁ መሆን ስላለበት የ20019 ዓ.ም የመማር ማስተማር ሂደት ፍፁም ሰላማዊ እንዲሆን በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ጥልቅ ውይይት መካሄዱን ተናግረዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲውን የመማር ማስተማር ሂደት ፍፁም ሰላማዊ ከማድረግ አንፃር ጥምር ኮሚቴው በጋራ የሚያከናውናቸው ተግባራት በዝርዝር ዕቅዱ ውስጥ መካተታቸውንና በዕቅዱ ላይ በተደረገው የጋራ ውይይትም ከመግባባት ላይ በመድረስ ውይይቱ የተጠናቀቀ መሆኑንም ከኮማንደር በየነ ዱሬሳ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡

–                               የህዝብ እና ዓለምአቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *