(ኮትዩ፣ ነሐሴ 29 ቀን 2018 ዓ.ም) – በሴኔት ስብሰባው ላይ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዘዳንት ዶ/ር ተሾመ ነቃጥበብ እንደገለጹት፣ ዩኒቨርሲቲው ቀደም ሲል በአንድ ዓይነት የሜጀር ፕሮግራም ሲያካሂድ የቆየውን መማር ማስተማር በማሻሻል፣ አንድ ለመምህርነት የሚሰለጥን ተማሪ በሁለት ዓይነት የትምህርት ዲሲፕሊን እንዲሰለጥን የሚያስችል በመሆኑ በዩኒቨርሲቲው ሕይወትም ሆነ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ኃላፊነት ነው ብለዋል፡፡
እንደ ፕሬዘዳንቱ ገለጻ ይህ የደብል ሜጀር መርሐግብር የሀገራችንን የትምህርት ጥራት ከፍ ለማድረግ፣ የመምህራንን አቅም ለማሳደግ፣ የመምህራንን እጥረት ለመቅረፍ፣ የመማር ማስተማሩ ሂደት ሳይበደል ውጤታማ ሥራዎችን ለመስራት የሚያግዝ ነው፡፡
የሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪ ፕሮግራሞችን ለማጠናከርና ለማስጀመር የሚያስችል አስፈላጊው ውይይት ተደርጎባቸው እንደሚፀድቁም የዩኒቨርሲቲው ፕሬዘዳንት ዶ/ር ተሾመ ነቃጥበብ ተናግረዋል፡፡
የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዘዳንት ዶ/ር አለባቸው ኬሚሶ በበኩላቸው፣ የዛሬው የሴኔት ስብሰባ በዩኒቨርሲቲው ታሪክ በጣም አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው የዩኒቨርሲቲውን ፕሮግራሞች የበለጠ ሳቢ፣ ተፈላጊ እና ዩኒቨርሲቲው ሀገራዊ ተልዕኮውን በአግባቡ እንዲወጣ የሚያግዙ ፕሮግራሞችን ከዲፓርትመንት ካውንስል ጀምሮ እስከ የሴኔት ስታንዳርድ ኮሚቴ ድረስ ደረጃ በደረጃ ውይይት በማድረግ፣ በመከለስና በማሻሻል እንዲሁም የውጪ ገምጋሚዎችን በማስገምገም በሰፊው እየታዩ የመጡና ለዛሬው የውሳኔ ቀን የደረሱ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
በዚሁ መሠረት ለሴኔት የቀረቡት 83 ፕሮግራሞች ሲሆኑ፣ ከነዚህም 23 የባችለር ኦፍ ኢጁኬሽን፣ 33 የማስተርስ ኦፍ ኢጁኬሽን፣ ወደ 19 የሚጠጉት ደግሞ የሦስተኛ ዲግሪ ፕሮግራሞች መሆናቸውን ዶ/ር አለባቸው አስረድተዋል፡፡
ሴኔቱ በቀረቡለት ፕሮግራሞች ላይ ሰፊና ገንቢ ውይይት በማድረግ እንደገና መሻሻል ያለባቸውን የማሻሻያ ሃሳብ በማቅረብ የአካዳሚክ ፕሮግራሞቹን አጽድቋል፡፡
– የህዝብ እና ዓለምአቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት
